የምትቀድሱት እርሱ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ የምትፈሩት እርሱ ይሁን፤ የምትንቀጠቀጡለትም እርሱ ይሁን።
የአብርሃም አምላክ፣ የናኮር አምላክ፣ የአባታቸውም አምላክ በመካከላችን ይፍረድብን”። ስለዚህ ያዕቆብ በአባቱ በይሥሐቅ ፍርሀት ማለ።
መፈራት ያለብህ አንተ ብቻ ነህ፤ በተቈጣህ ጊዜ ማን በፊትህ መቆም ይችላል?
ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሀት ከእናንተ ጋራ ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው።
በመካከላቸው የእጄ ሥራ የሆኑ፣ ልጆቻቸውን ሲያዩ፣ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብን ቅዱስ ቅድስና ያውቃሉ፤ በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሀት ይቆማሉ።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍትሕ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ ቅድስናውን በጽድቅ ይገልጻል።
ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ሆነህ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፤ በፊታቸው ቅድስናዬን ስገልጥ ሕዝቦች እኔን ያውቁ ዘንድ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር፦ “ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣ ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣ እከበራለሁ’ ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ።
ቅዱሱን ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ቅዱስ መሆኔ በእስራኤላውያን ዘንድ ይታወቅ፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
“ከርሱ ጋራ የገባሁት ኪዳን የሕይወትና የሰላም ኪዳን ነበር፤ እነርሱንም ሰጠሁት፤ ይህም ክብርን አመጣ፤ እርሱም አከበረኝ፤ ስሜን በመፍራትም ጸና።
ምክንያቱም ማኅበረ ሰቡ በጺን ምድረ በዳ ባለው ውሃ አጠገብ ባመፁ ጊዜ እኔን በሕዝቡ ፊት ቅዱስ አድርጋችሁ ለማክበር ሁለታችሁም ትእዛዜን ስላልጠበቃችሁ ነው።” ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ የመሪባ ውሃ ነው።
ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።
ነገር ግን መፍራት የሚገባችሁን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ አዎን፣ እርሱን ፍሩት እላችኋለሁ።
ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤
ምን ጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላ።
ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና። የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ።”
ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቈራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፣ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቈራረጣል” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ።