እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን? እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
“አክዓብ ራሱን በፊቴ እንዴት እንዳዋረደ አየህን? ራሱን ስላዋረደ ይህን መከራ በዘመኑ አላመጣበትም፤ ነገር ግን ይህን በቤቱ ላይ የማመጣው በልጁ ዘመን ነው።”
ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ለንጉሡ፣ “ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም ለንጉሡ ከመጽሐፉ አነበበለት።
ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።
አሁንም እንደ ጌታዬ ምክርና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩ ሰዎች እነዚህን ሴቶችና ልጆቻቸውን ለመስደድ በአምላካችን ፊት ቃል ኪዳን እንግባ፤ በሕጉም መሠረት ይፈጸም።
በደል ከፈጸሙት ምርኮኞች የተነሣም በእስራኤል አምላክ ቃል የተንቀጠቀጡት ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ እጅግ እንደ ደነገጥሁ በዚያው ተቀመጥሁ።
ሥጋዬ አንተን በመፍራት ይንቀጠቀጣል፤ ፍርድህንም እፈራለሁ።
ገዦች ያለ ምክንያት አሳደዱኝ፤ ልቤ ግን ከቃልህ የተነሣ እጅግ ፈራ።
እግዚአብሔር በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል።
እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።
እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።
እግዚአብሔርን ዘወትር የሚፈራ ሰው ብፁዕ ነው፤ ልቡን የሚያደነድን ግን መከራ ላይ ይወድቃል።
ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብርን ይጐናጸፋል።
ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።
ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣ የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣ በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።
ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋራ እሆናለሁ።
የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።
እናንተ በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣ ይህን የእግዚአብሔር ቃል ስሙ፤ “እናንተ ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣ ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣ ‘እስኪ እግዚአብሔር ይክበርና፣ የእናንተን ደስታ እንይ!’ አሏችሁ፤ ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።
እግዚአብሔርን ይከተላሉ፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ እርሱ ሲያገሣ፣ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ።
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤ እግሬም ተብረከረከ፤ ሆኖም በሚወርረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣ የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።
ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ከቤተ መቅደስ የሚበልጥ በዚህ አለ።
እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?’
ነገር ግን ተነሣና ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል።”
ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤
እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው።