መንግሥታት ጽድቅሽን፣ ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣ በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።
እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን።
ከእንግዲህ ወዲያ ስምህ አብራም መባሉ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁና።
ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም፣ ከሰዎችም ጋራ ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው።
እግዚአብሔር ማዳኑን አሳወቀ፤ ጽድቁንም በሕዝቦች ፊት ገለጠ።
ፈራጆችሽን እንደ ጥንቱ፣ አማካሪዎችሽንም እንደ ቀድሞው እመልሳለሁ፤ ከዚያም የጽድቅ መዲና፣ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።”
በእምነቱ የጸና ጻድቅ የሆነ ሕዝብ ይገባ ዘንድ፣ በሮቿን ክፈቱ።
በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።”
ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣ እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፤ እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።”
እርሱም፣ “ባሪያዬ መሆንህ፣ የያዕቆብን ነገዶች እንደ ገና መመለስህ፣ የጠበቅኋቸውን እስራኤል መልሰህ ማምጣት ለአንተ ቀላል ነገር ነው፤ ድነቴን እስከ ምድር ዳርቻ እንድታመጣ፣ ለአሕዛብ ብርሃን አደርግሃለሁ” አለኝ።
እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ የተቀደሰ ክንዱን ይገልጣል፤ በምድር ዳርቻዎች ያሉ ሁሉ፣ የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።
በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።
በሮችሽ ምን ጊዜም የተከፈቱ ይሆናሉ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ አይዘጉም፤ ይህም ሰዎች የመንግሥታትን ብልጽግና ወደ አንቺ እንዲያመጡ፣ ነገሥታታቸውም በድል ወደ አንቺ እንዲገቡ ነው።
የመንግሥታትን ወተት ትጠጪያለሽ፤ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣ ቤዛሽም እኔ የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።
ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣ ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።
ዘሮቻቸው በመንግሥታት፣ ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ፤ የሚያዩአቸውም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የባረካቸው ሕዝብ እንደ ሆኑ ያውቃሉ።”
እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም የምትፈለግ፣ ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።
ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ ነገር ግን፣ “ደስታዬ በርሷ” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፣ “ባለባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባለባል ትሆናለች።
ስማችሁንም፣ የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤ ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል።
ከሚያጽናኑ ጡቶቿ፣ ትጠባላችሁ፤ ትረካላችሁም፤ እስክትረኩም ትጠጣላችሁ፤ በተትረፈረፈ ሀብቷም ትደሰታላችሁ።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ሰላምን እንደ ወንዝ ውሃ አፈስስላታለሁ፤ የመንግሥታትንም ብልጽግና እንደ ጅረት ውሃ አጐርፍላታለሁ፤ ትጠባላችሁ፤ በዕቅፏም ትያዛላችሁ፤ በጭኖቿም ላይ ትፈነድቃላችሁ።
“በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶቤልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ።
በዚያ ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት ትኖራለች፤ የምትጠራበትም ስም፣ “እግዚአብሔር ጽድቃችን” የሚል ይሆናል።’
ይህች ከተማ፣ ለርሷ ያደረግሁትን በጎ ነገር ሁሉ በሚሰሙት የምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ለዝና፣ ለደስታ፣ ለምስጋናና ለክብር ትሆናለች፤ ከምሰጣትም የተትረፈረፈ ብልጽግናና ሰላም የተነሣ ይፈራሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም።’
በዱር አራዊት መካከል እንዳለ አንበሳ፣ በእግሩ እየጨፈላለቀ እንደሚሄድ፣ የሰበረውን ማንም ሊነጥቀው እንደማይችል፣ በበግ መንጋ መካከል እንዳለ፣ እንደ ደቦል አንበሳ ሁሉ፣ የያዕቆብም ትሩፍ፣ በአሕዛብ ዘንድ፣ በብዙም ሕዝብ መካከል እንደዚሁ ይሆናል።
ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። ሁለቱም እዚያ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ጋራ በመሆን አንድ ዓመት ሙሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ “ክርስቲያን” ተብለው ተጠሩ።
ይኸውም ክርስቶስ መከራን እንደሚቀበልና ከሙታን ቀዳሚ ሆኖ በመነሣት ለሕዝቡና ለአሕዛብ ብርሃንን እንደሚሰብክ ነው።”
ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ! ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤
ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ ደግሞም ከሚቀበለው ሰው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይ እሰጠዋለሁ።
ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም። የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ይኸውም ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም በርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ አዲሱን ስሜንም በርሱ ላይ እጽፋለሁ።