ዕለት በዕለት ይፈልጉኛል፤ መንገዴን ለማወቅ የሚጓጉ ይመስላሉ፤ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ፣ የአምላኩንም ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ሁሉ፣ ተገቢ የሆነ ፍትሕ ይለምኑኛል፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ እንዲቀርብ የሚወድዱም ይመስላሉ።
ድንጋጌህን አሰላስላለሁ፤ ልቤን በመንገድህ ላይ ጥያለሁ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ቅርብ ነህ፤ ትእዛዞችህም ሁሉ እውነት ናቸው።
ከምድር ላይ ሊያስወግዱኝ ጥቂት ቀራቸው፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አልተውሁም።
እግዚአብሔር የክፉዎችን መሥዋዕት ይጸየፋል፤ የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሠኘዋል።
ዐመፀኞችና ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይደቅቃሉ፤ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ።
እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፣ በደል የሞላበት ወገን፣ የክፉ አድራጊ ዘር፣ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃልለዋል፤ ጀርባቸውንም በርሱ ላይ አዙረዋል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ የሚያመልከኝም፣ ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው።
ብዙ ነገርን አያችሁ፤ ነገር ግን አላስተዋላችሁም፤ ጆሯችሁ ክፍት ነው፤ ነገር ግን ምንም አትሰሙም።”
ጽድቅሽንና ሥራሽን አጋልጣለሁ፤ እነርሱም አይጠቅሙሽም።
“እናንተ የአስማተኛዪቱ ልጆች ግን፣ እናንተ የአመንዝራውና የጋለሞታዪቱ ዘር፤ እናንተ፣ ወዲህ ኑ!
በእግዚአብሔር ላይ ዐምፀናል፤ ሐሰት ተናግረናል፤ አምላካችንን ከመከተል ዘወር ብለናል፤ ዐመፃንና ግፍን አውርተናል፤ ልባችን የፀነሰውን ውሸት ተናግረናል።
ነቢዩ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፤ “ቀድሞ ብዙዎች ነበርን አሁን እንደምታየን ግን የቀረነው ጥቂት ነን፤ ስለዚህ እባክህ ልመናችንን ስማ፤ ለዚህ ለተረፈው ሕዝብ ሁሉ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ።
‘ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ እርሱ ያለህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እንታዘዛለን’ ብላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር በላካችሁኝ ጊዜ ሕይወታችሁን የሚያጠፋ ስሕተት ፈጸማችሁ።
ስሜ ወደሚጠራበት ወደዚህ ቤት መጥታችሁ በፊቴ ትቆሙና “ደኅና ነን” እያላችሁ እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ታደርጋላችሁ።
“ ‘ትሰርቃላችሁ፤ ሰው ትገድላላችሁ፤ ታመነዝራላችሁ፤ በሐሰት ትምላላችሁ፤ ለበኣል ታጥናላችሁ፤ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ትከተላላችሁ፤
“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሐሳቤን ልትጠይቁ መጣችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ ከእኔ ጠይቃችሁ እንድትረዱ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’
የእግዚአብሔርን ቀን ለምትሹ፣ ለእናንተ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትሻላችሁ? ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።
እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛ ሰው መሆንህን፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉንም እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ይልቁንስ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?
ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር።
ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሠኙ ወደዳችሁ።
እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ የማይበቁ ናቸው።
ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።