እግዚአብሔር ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ፀሓይ ባቃጠለው ምድር ፍላጎትህን ያሟላል፤ ዐጥንትህን ያበረታል፤ በውሃ እንደ ረካ የአትክልት ቦታ፣ እንደማይቋርጥም ምንጭ ትሆናለህ።
በራብ ጊዜ ከሞት፣ በጦርነትም ከሰይፍ ያድንሃል።
እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና፤ የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቧል።
ዝቅ ያሉትን በፍትሕ ይመራቸዋል፤ ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል።
አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።
በዚህም ነፍሳቸውን ከሞት ያድናል፤ በራብ ዘመንም በሕይወት ያኖራቸዋል።
በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።
ይህ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችን ነውና፤ እስከ መጨረሻው የሚመራንም እርሱ ነው።
በምክርህ መራኸኝ፤ ኋላም ወደ ክብር ታስገባኛለህ።
ከኀይል ወደ ኀይል ይሸጋገራሉ፤ እያንዳንዱም በጽዮን ባለው አምላክ ፊት ይቀርባል።
ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።
ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል።
ሰነፍ አጥብቆ ይመኛል፤ አንዳችም አያገኝም፤ የትጉሆች ምኞት ግን ይረካል።
ሥሥታም ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይባረካል።
ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣ ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል።
አንቺ የአትክልት ቦታ ፏፏቴ፣ ከሊባኖስ የሚወርድ፣ የፈሳሽ ውሃ ጕድጓድ ነሽ።
እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ዘወትር ውሃ አጠጣዋለሁ፤ ስለዚህ ማንም አይጐዳውም፣ ቀንና ሌሊት እጠብቀዋለሁ፤
ይህ ሰው በከፍታ ላይ ይኖራል፤ የተራራም ምሽግ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራ ይሰጠዋል፣ ውሃውም አይቋረጥበትም።
“ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ ጕረሯቸው በውሃ ጥም ደርቋል። ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤ እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።
እነርሱም በለመለመ መስክ ላይ እንደ ሣር፣ በወንዝ ዳር እንደ አኻያ ዛፍ ይበቅላሉ።
አይራቡም፤ አይጠሙም፤ የምድረ በዳ ትኵሳት ወይም የፀሓይ ቃጠሎ አይጐዳቸውም። የሚራራላቸው ይመራቸዋል፤ በውሃ ምንጭ ዳርም ያሰማራቸዋል።
መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እመልሳለሁ፤
ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣ ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።
ይህን ስታዩ፣ ልባችሁ ሐሤት ያደርጋል፤ ዐጥንቶቻችሁም እንደ ሣር ይለመልማሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከባሮቹ ጋራ መሆኑ ይታወቃል፤ ቍጣው ግን በጠላቶቹ ላይ ይገለጣል።
በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደ ለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”
መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣ በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣ በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህም አያዝኑም።
እነርሱም፣ “ጠፍ የነበረው ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት መሰለ፤ የተደመሰሱ፣ የፈራረሱና ባድማ የሆኑት ከተሞች አሁን መኖሪያና ምሽግ ሆነዋል” ይላሉ።
በምድረ በዳ፣ በሐሩር ምድርም ተንከባከብሁህ።
የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤
እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት ውሃ ምንጭ ይሆናል።”
በእኔ የሚያምን፣ መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሃ ምንጭ ከውስጡ ይፈልቃል።”
ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤
አሁንም ራሱ አምላካችንና አባታችን፣ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ እንድንመጣ መንገዳችንን ያቅናልን።