በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ።
በዘመኑም ፍጻሜ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ ከተራሮች ከፍ ብሎ ይመሠረታል፤ ከኰረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ።
ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ በጐዳናውም እንድንሄድ፤ መንገዱን ያስተምረናል።” ሕግ ከጽዮን፣ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
በዚያ ቀን ይህ መዝሙር በይሁዳ ምድር ይዘመራል፤ ብርቱ ከተማ አለችን፤ አምላካችን ቅጥሮቿንና ምሽጎቿን፣ ለድነት አድርጓል።
በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።”
ዘርህ እንደ አሸዋ፣ ልጆችህ ስፍር እንደሌለው ትቢያ በሆኑ ነበር፤ ስማቸው አይወገድም፤ ከፊቴም አይጠፋም።”
በእሾኽ ፈንታ የጥድ ዛፍ፣ በኵርንችት ፈንታ ባርሰነት ይበቅላል። ይህም የእግዚአብሔር መታሰቢያ፣ ሊጠፋ የማይችል፣ የዘላለም ምልክት ይሆናል።”
ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ። የሚቃጠል መሥዋዕታቸውንና ሌሎች መሥዋዕቶቻቸውን፣ በመሠዊያዬ ቢሠዉ እቀበላቸዋለሁ፤ ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።”
ከእንግዲህ በምድርሽ ሁከት፣ በጠረፎችሽም ጥፋትና መፈራረስ አይሰማም፤ ነገር ግን ቅጥሮችሽን ድነት፣ በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያቸዋለሽ።
እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም የምትፈለግ፣ ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።
መንግሥታት ጽድቅሽን፣ ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣ በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።
ለእግዚአብሔር ቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላል እግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቍርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል።
“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤
በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር።
አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አያሸንፏትም።
ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ሰጣቸው።
እናንተም ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ ዐብራችሁ እየተገነባችሁ ነው።
ይህንም የምጽፍልህ ብዘገይ እንኳ ሰዎች በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንድታውቅ ነው፤ ቤቱም የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው።
ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን።
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው።
መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ ደግሞም ከሚቀበለው ሰው በቀር ማንም የማያውቀው አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይ እሰጠዋለሁ።
ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ውስጥ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም። የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም ይኸውም ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም ስም በርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ አዲሱን ስሜንም በርሱ ላይ እጽፋለሁ።
ድል የሚነሣም እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ እኔም በአባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም።
ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር።