ሕዝቤን ተቈጥቼ ነበር፤ ርስቴን አርክሼው ነበር፤ አሳልፌ በእጅሽ ሰጠኋቸው፤ አንቺ ግን አልራራሽላቸውም፤ በዕድሜ በገፉት ላይ እንኳ፣ እጅግ ከባድ ቀንበር ጫንሽባቸው።
ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ።
አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”
ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚያ ስለ ነበር፣ ሰራዊቱ ወደ ሰማርያ በተመለሰ ጊዜ ለመቀበል ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ እናንተ ግን እስከ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ፈጃችኋቸው።
ስለዚህ የባቢሎናውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ፈጀ፤ ወጣቱንም ሆነ ወጣቲቱን፣ ሽማግሌውንም ሆነ በዕድሜ የገፋውን አላስቀረም፤ እግዚአብሔር ሁሉንም ለናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጠው።
ከሰይፍ የተረፉትን ቅሬታዎች በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ እስከ ፋርስ መንግሥት መነሣትም ድረስ የእርሱና የልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ።
ነገር ግን አባቶቻችን የሰማይን አምላክ አስቈጥተውት ስለ ነበር፣ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለከለዳዊው ናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤተ መቅደስ አፈራርሶ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ።
አንተ የመታሃቸውን አሳድደዋልና፤ ያቈሰልሃቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል።
ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፣ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፣ እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፣ አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፣ በሚያስቈጣኝም ሕዝብ ላይ እሰድደዋለሁ።
ዐይናቸው እያየ ሕፃናታቸው ይጨፈጨፋሉ፤ ቤታቸው ይዘረፋል፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።
ዓለምን ምድረ በዳ ያደረገ፤ ከተሞችን ያፈራረሰ፣ ምርኮኞቹንም ወደ አገራቸው እንዳይሄዱ የከለከለ ይህ ነውን?”
ሕዝቦችን በማያቋርጥ ቍጣ የመታውን፣ ያለ ርኅራኄ እያሳደደ የቀጠቀጠውን ሰብሯል።
ስለዚህ የመቅደስህን አለቆች አዋርዳለሁ፤ ያዕቆብን ለጥፋት፣ እስራኤልን ለስድብ እዳርጋለሁ።
ቀስትና ጦር ይዘዋል፤ ጨካኞች ናቸው፤ ምሕረትም አያደርጉም፤ በፈረሳቸው እየጋለቡ ሲመጡ፣ ድምፃቸው እንደ ባሕር ሞገድ ይተምማል፤ ያስገመግማል። አንቺ የባቢሎን ሴት ልጅ ሆይ፤ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ተዋጊዎች ይመጡብሻል።
“ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤ በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤ በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤ ኀይሌንም አዳከመ፤ ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣ እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ።
“ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ፤ የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም፤ ጠላቶቼ ሁሉ ጭንቀቴን ሰሙ፤ አንተ ባደረግኸውም ደስ አላቸው፤ አቤቱ የተናገርሃት ቀን ትምጣ፤ እነርሱም እንደ እኔ ይሁኑ።
የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ፣ ጌታ ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤ የይሁዳን ሴት ልጅ ምሽጎች፣ በቍጣው አፈረሳቸው፤ መንግሥቷንና መሳፍንቷን፣ በማዋረድ ወደ ምድር ጣላቸው።
እግዚአብሔር ራሱ በትኗቸዋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤ ካህናቱ አልተከበሩም፤ ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም።
መሳፍንት በእነርሱ እጅ ተሰቀሉ፤ ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።
ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።
ንግድህ ስለ ደረጀ፣ በዐመፅ ተሞላህ፣ ኀጢአትም ሠራህ፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ተራራ በውርደት አሳደድሁህ፤ ጠባቂ ኪሩብ ሆይ፤ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አስወጣሁህ።
በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፣ በዕፍረት ትሸፈናለህ፤ ለዘላለምም ትጠፋለህ።
እናንተ በቅዱሱ ተራራዬ እንደ ጠጣችሁ፣ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፤ ይጠጣሉ፤ አብዝተውም ይጠጣሉ፤ ከዚህም በፊት እንዳልሆኑት ይሆናሉ።
ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ፣ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ።
ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’
በምትፈርዱበትም ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል።
ሽማግሌ የማያከብር፣ ለብላቴና የማይራራ፣ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው።
ምክንያቱም ምሕረት ያላደረገ ሁሉ ያለ ምሕረት ይፈረድበታል፤ ምሕረት በፍርድ ላይ ያይላል።