“እናንተ ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤ ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤ ምድር ትከፈት፤ ድነት ይብቀል፤ ጽድቅም ዐብሮት ይደግ፤ እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።
“ ‘ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣ አልሰማህምን? ጥንትም እንዳቀድሁት፣ አሁን ግን እንዲፈጸም አደረግሁት፤ ይህም የተመሸጉትን ከተሞች፣ አንተ የድንጋይ ክምር ማድረግህ ነው።
በሲና አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ በእስራኤል አምላክ፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ሰማያትም ዶፍ አወረዱ።
ተራሮች ብልጽግናን፣ ኰረብቶችም የጽድቅን ፍሬ ለሕዝቡ ያመጣሉ።
እንደ ዝናብ በታጨደ መስክ ላይ ይወርዳል፤ እንደ ካፊያም ምድርን ያረሰርሳል።
ከእሴይ ግንድ ቍጥቋጥ ይወጣል፤ ከሥሮቹም አንዱ ቅርንጫፍ ፍሬ ያፈራል።
ይህም የሚሆነው መንፈስ ከላይ እስኪፈስስልን፣ ምድረ በዳው ለም መሬት፣ ለሙ መሬትም ጫካ እስኪመስል ድረስ ነው።
በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ዛፍ ቅርንጫፍ ያማረና የከበረ ይሆናል፤ የምድሪቱም ፍሬ ከጥፋት ለተረፈው የእስራኤል ወገን ኵራትና ክብር ይሆናል።
“ከማሕፀን የሠራህ፣ የተቤዠህም፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሁሉን ነገር የፈጠርሁ፣ ብቻዬን ሰማያትን የዘረጋሁ፣ ምድርን ያንጣለልሁ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
በተጠማ ምድር ላይ ውሃ፤ በደረቅ መሬት ላይ ወንዞችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ፣ በረከቴንም በልጅ ልጅህ ላይ አወርዳለሁ።
ጽድቄን እያመጣሁ ነው፤ ሩቅም አይደለም፤ ማዳኔም አይዘገይም። ለጽዮን ድነትን፣ ለእስራኤል ክብሬን አጐናጽፋለሁ።
ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።
በፊቱ እንደ ቡቃያ፣ ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤ የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤ እንድንወድደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም።
ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤ ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣ የእጆቼ ሥራ፣ እኔ የተከልኋቸው ቍጥቋጦች ናቸው።
ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣ ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤
አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፤ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ይፈጥራል፤ ሴት በወንድ ላይ ከበባ ታደርጋለች።”
እነርሱንና በኰረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች እባርካለሁ። በወቅቱም ዝናብ አወርድላቸዋለሁ፤ ዝናቡም የበረከት ዝናብ ይሆናል።
ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና።
“በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤ ኰረብቶችም ወተት ያፈስሳሉ፤ በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎች ሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤ የሰጢምን ሸለቆ ያጠጣል።
ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።
ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።