የእጅ ጥበብ ባለሙያው የወርቅ አንጥረኛውን ያበረታታዋል፤ በመዶሻ የሚያሳሳውም፣ በመስፍ ላይ የሚቀጠቅጠውን ያነቃቃዋል፤ ስለ ብየዳም ሥራው፣ “መልካም ነው” ይለዋል፤ የጣዖቱ ምስል እንዳይወድቅም በምስማር ያጣብቀዋል።
እያንዳንዱ ይረዳዳል፤ ወንድሙንም፣ “አይዞህ!” ይለዋል።
የተጠፈጠፈ ብር ከተርሴስ፣ ወርቅም ከአፌዝ ይመጣል። የእጅ ጥበብ ባለሙያና አንጥረኛው የሠሯቸው፣ ብልኀተኞችም ያበጇቸው ሁሉ፣ ሰማያዊና ሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፈዋል።
እርሱም፣ “እንዴት፣ ‘ምን ሆንህ’ ብላችሁ ትጠይቁኛላችሁ? የሠራኋቸውን አማልክቴንና ካህኔን ወስዳችሁ ሄዳችኋል፤ ምን የቀረኝ ነገር አለ?” አላቸው።