የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፤ “በምድረ በዳ የጌታን መንገድ፣ አዘጋጁ፤ ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣ በበረሓ አስተካክሉ።
ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ለስሙም ተቀኙ፤ በደመናት ላይ የሚሄደውን ከፍ አድርጉት፤ ስሙ እግዚአብሔር በተባለው ፊት፣ እጅግ ደስ ይበላችሁ።
በዚያ አውራ ጐዳና ይሆናል፤ የተቀደሰ መንገድ ተብሎ ይጠራል። የረከሱ አይሄዱበትም፤ በመንገዱ ላይ ላሉት ብቻ ይሆናል፤ ቂሎችም አይሄዱም።
ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው ምድር ይስተካከላል፤ ወጣ ገባውም ለጥ ያለ ሜዳ ይሆናል።
እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤
ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።
እንዲህ ይባላል፤ “አብጁ፤ አብጁ፤ መንገድ አዘጋጁ! ከሕዝቤ መንገድ ዕንቅፋት አስወግዱ።”
“እነሆ፤ በፊቴ መንገድ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበትም የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ይመጣል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ዮሐንስም በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተነገረው፣ “ ‘ለጌታ መንገድ አቅኑለት’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ድምፅ እኔ ነኝ” ሲል መለሰ።