አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ።
ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።
መዓትህን ሁሉ አራቅህ፤ ከብርቱ ቍጣህም ተመለስህ።
እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ለሕዝቡ፣ ለቅዱሳኑ ሰላምን ይናገራልና፤ ዳሩ ግን ወደ ከንቱ ምግባራቸው አይመለሱ።
ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤
በዚያ ቀን እንዲህ ትላለህ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ቀድሞ ተቈጥተኸኝ ነበር፤ አሁን ግን ከቍጣህ ተመለስህ፤ ደግሞም አጽናንተኸኛልና አወድስሃለሁ።
ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና።
በመጀመሪያ፣ ‘እነሆ፤ ተመልከቺአቸው!’ ብዬ ለጽዮን የተናገርሁ እኔ ነበርሁ፤ ለኢየሩሳሌምም የምሥራች ነጋሪን ሰጥቻለሁ።
ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው? ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣ ብርሃንም ከሌለው፣ በእግዚአብሔር ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ።
“የማጽናናችሁ እኔ፣ እኔው ብቻ ነኝ፤ ሟች የሆኑትን ሰዎች፣ እንደ ሣር የሚጠወልጉትን የሰው ልጆች ለምን ትፈራለህ?
እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤ ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣ በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤ ተድላና ደስታ፣ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በርሷ ይገኛሉ።
እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች፣ በአንድነት በእልልታ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቷል፤ ኢየሩሳሌምንም ተቤዥቷልና።
“ብርሃንሽ መጥቷልና ተነሺ አብሪ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል።
የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት፣ የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣ የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤
በዚህም በአንቺ ላይ የነበረው ቍጣዬ ይበርዳል፤ የቅናቴ ቍጣም ከአንቺ ይርቃል። እኔም ዝም እላለሁ፤ ከእንግዲህም አልቈጣም።
እግዚአብሔርም ከእኔ ጋራ ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሠኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት።
“ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፤ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፤ እልል በዪ፤ እነሆ፤ ጻድቁና አዳኙ ንጉሥሽ፣ ትሑት ሆኖ፣ በአህያ ላይ ተቀምጦ፣ በአህያ ግልገል፣ በውርንጫዪቱ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል።
እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።