አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ መሆንህን ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”
አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ።
በየዕለቱም ባሪያውንና ሕዝቡን እስራኤልን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እንዲረዳቸው፣ ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያቀረብኋት የራሴ ልመና በቀንና በሌሊት ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት ትቅረብ።
ይኸውም የምድር ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደ ሆነና ከርሱ በቀር ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ነው።
“ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”
በቍጣ አጥፋቸው፤ ፈጽመህም አስወግዳቸው፤ በዚህም እግዚአብሔር የያዕቆብ ገዥ መሆኑ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ይታወቃል። ሴላ
በዚያ ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤ አምላካችን ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ በርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ የሚያድነንም እርሱ ነውና።
የሚፈራ ልብ ላላቸው እንዲህ በሉ፤ “በርቱ፤ አትፍሩ፤ አምላካችሁ ይመጣል፤ ሊበቀል ይመጣል፤ እርሱም ብድራቱን ይዞ፣ ሊያድናችሁ ይመጣል።”
“በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።
“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው! ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።
እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔ በቀር አምላክ የለም። አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣ እኔ አበረታሃለሁ።
በአሕዛብ መካከል የረከሰውን፣ እናንተ በእነርሱ ዘንድ ያረከሳችሁትን፣ የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ ከዚያም ዐይኖቻቸው እያዩ፣ በእናንተ አማካይነት ራሴን ቅዱስ አድርጌ ስገልጥ፣ አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
“ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ።
በእግዚአብሔር ፊት የሚያገለግሉ ካህናት፣ በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አደባባይ መካከል ሆነው ያልቅሱ፤ እንዲህም ይበሉ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አድን፤ ርስትህን በአሕዛብ መካከል መተረቻ፣ መሣቂያና መሣለቂያም አታድርግ፤ ለምንስ በሕዝቦች መካከል፣ ‘አምላካቸው ወዴት ነው?’ ይበሉን።”
“ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ በየስፍራውም ሁሉ ለስሜ ዕጣንና ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።