እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፤ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል የሰበረውን ይዞ ሲያገሣ፣ ብዙ እረኞች ተጠራርተው ሲመጡበት፣ ጩኸታቸው እንደማያስፈራው፣ በድምፃቸውም እንደማይታወክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በከፍታዎቿ ላይ ለውጊያ እንዲሁ ይወርዳል።
እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡ።
እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።”
መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤ ግብጻውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብጽን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ።
ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤ ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳት ይለኰሳል።
የጽዮን ሕዝብ ሆይ፤ እልል በሉ፤ በደስታም ዘምሩ፤ በመካከላችሁ ያለው የእስራኤል ቅዱስ ታላቅ ነውና።”
እግዚአብሔር በሚነድድ ቍጣና በሚባላ እሳት፣ በወጀብና በነጐድጓድ፣ በበረዶም ድንጋይ፣ ግርማ የተሞላበትን ድምፁን ሰዎች እንዲሰሙ አድርጎ ያሰማል፤ ክንዱም ስትወርድ ያሳያቸዋል።
እግዚአብሔር የሚያወርድባቸው የቅጣት በትር ሁሉ፣ በከበሮና በበገና ድምፅ የታጀበ ነው፤ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ መታቸው።
እግዚአብሔር እንደ ኀያል ሰው ይዘምታል፤ እንደ ተዋጊ በቅናት ይነሣል፤ የቀረርቶ ጩኸት ያሰማል፤ ጠላቶቹንም ድል ያደርጋል።
አንበሳ ከዮርዳኖስ ደኖች ድንገት ወጥቶ፣ ወደ ግጦሽ ሜዳ ብቅ እንደሚል፣ እኔም ባቢሎንን ሳይታሰብ ከምድሯ አባርራታለሁ፤ የመረጥሁትንም በርሷ ላይ እሾማለሁ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ማንስ ሊገዳደረኝ ይችላል? የትኛውስ እረኛ ሊቋቋመኝ ይችላል?”
እግዚአብሔርን ይከተላሉ፤ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ እርሱ ሲያገሣ፣ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ።
አንበሳ አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?
ከመካከላቸው እጅግ ደካማ የሆነው እንደ ዳዊት፣ የዳዊት ቤትም ፊት ፊታቸው እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንደ አምላክ ይሆንላቸው ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን እግዚአብሔር ይከልላቸዋል።
እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል።
እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፣ ‘በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ።’
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ይከልላቸዋል፤ ጠላቶቻቸውን ይደመስሳሉ፤ በድንጋይ ወንጭፍም ያሸንፋሉ፤ ይጠጣሉ፤ በወይን ጠጅ እንደ ሰከረ ሰው ይጮኻሉ፤ የመሠዊያውን ማእዘኖች ለመርጨት፣ እንደ ተዘጋጀ ዕቃ፣ እነርሱም እንደዚሁ ተሞልተዋል።
እኔ ግን ቤቴን ከዘራፊ ኀይሎች እጠብቃለሁ፤ ጨቋኝ ከእንግዲህ ሕዝቤን አይወርስም፤ አሁን ነቅቼ እጠብቃለሁና።
እንደሚያገሣ አንበሳም ድምፁን ከፍ አድርጎ ጮኸ፤ በጮኸም ጊዜ የሰባቱ ነጐድጓዶች ድምፆች ተናገሩ።
ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቷል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” አለኝ።