እነዚህም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለመስማት የማይፈልጉ፣ ዐመፀኛ ሕዝቦችና አታላይ ልጆች ናቸው።
እግዚአብሔር ለምናሴና ለሕዝቡ ተናገረ፤ እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።
ነገር ግን እንደ አባቶቻቸው፣ እልኸኞችና ዐመፀኞች፣ ልቡን ያላቀና፣ መንፈሱም በእግዚአብሔር የማይታመን ትውልድ አይሆኑም።
ስለዚህ በገዛ ዕቅዳቸው እንዲሄዱ፣ አሳልፌ ለደንዳናው ልባቸው ሰጠኋቸው።
ሕግን ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው።
እናንተ የሰዶም ገዦች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሰዎች፤ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።
ሰማያት ሆይ፤ ስሙ! ምድር ሆይ፤ አድምጪ! እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናግሯልና፤ “ልጆች ወለድሁ፣ አሳደግኋቸውም፤ እነርሱ ግን ዐመፁብኝ።
እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፣ በደል የሞላበት ወገን፣ የክፉ አድራጊ ዘር፣ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃልለዋል፤ ጀርባቸውንም በርሱ ላይ አዙረዋል።
“የቍጣዬ በትር ለሆነ፣ የመቅሠፍቴም ዱላ በእጁ ላለው ለአሦራዊው ወዮለት!
ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፣ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፣ እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፣ አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፣ በሚያስቈጣኝም ሕዝብ ላይ እሰድደዋለሁ።
ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ ሕግን ጥሰዋል፤ ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል።
እናንተ፣ “ከሞት ጋራ ቃል ኪዳን ገብተናል፤ ከሲኦልም ጋራ ስምምነት አድርገናል፤ ውሸትን መጠጊያችን፣ ሐሰትን መደበቂያችን አድርገናል፤ ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ ሊነካን አይችልም” በማለት ታብያችኋል።
“ለዐመፀኞች ልጆች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር፤ “የእኔ ያልሆነውን ሐሳብ ይከተላሉ፤ ከመንፈሴ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ በኀጢአት ላይ ኀጢአት ይጨምራሉ።
የቱን ያህል እልኸኛ እንደ ነበርህ ዐውቃለሁና፤ የዐንገትህ ጅማት ብረት፣ ግንባርህም ናስ ነበር።
ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣ የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤ የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃልለዋል።
እርሱም፣ “ርግጥ ነው፤ እነርሱ ሕዝቤ ናቸው፤ የማይዋሹኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው” አለ። ስለዚህም አዳኝ ሆነላቸው።
ለዐመፀኛ ሕዝብ፣ መልካም ባልሆኑ መንገዶች ለሚሄዱ፣ የልባቸውን ምኞት ለሚከተሉ፣ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ። ዘወትር በፊቴ የሚያስቈጡኝ ሕዝቦች፣
‘የሬካብ ልጅ ኢዮናዳብ ልጆቹ የወይን ጠጅ እንዳይጠጡ አዘዛቸው፤ ይህም ትእዛዝ ተጠብቋል፤ የአባታቸውን ትእዛዝ ስለ ጠበቁ እስከ ዛሬ ድረስ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤ እናንተ ግን እኔ ደጋግሜ ብናገራችሁም፤ አልታዘዛችሁኝም።
እነዚህን ሁሉ ስታደርጉ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ደጋግሜ ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አላደመጣችሁኝም፤ ጠራኋችሁ፤ እናንተ ግን አልመለሳችሁም።
ስለዚህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ይህ ሕዝብ አምላኩን እግዚአብሔርን ያልታዘዘ፣ ምክሩን ያልተቀበለ ወገን ነው፤ እውነት ጠፍቷል፤ ከአንደበታቸውም ሸሽቷል።
“ሐሰትን ለመናገር፣ ምላሳቸውን እንደ ቀስት ገተሩ፤ በእውነት ሳይሆን፣ በሐሰት በምድሪቱ ገነኑ፤ ከክፋት ወደ ክፋት ሄዱ፤ እኔንም አላወቁኝም፤” ይላል እግዚአብሔር።
ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ ብለህ ተምሳሌት ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘ብረት ድስት በእሳት ላይ ጣድ፤ ከጣድህም በኋላ ውሃ ጨምርበት።
በዚያ ያለው ርግማን፣ መዋሸት፣ መግደል፣ መስረቅና ማመንዘር ብቻ ነው፤ ቃል ኪዳንን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ ደም ማፍሰስና ግድያ ይበዛል።
እርሷ ለማንም አትታዘዝም፤ የማንንም ዕርምት አትቀበልም፤ በእግዚአብሔር አትታመንም፤ ወደ አምላኳም አትቀርብም።
“እናንተ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ! ዐንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ።
እርሱም፣ “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ” አለ፤ ጠማማ ትውልድ፣ የማይታመኑም ልጆች ናቸውና።
ነገር ግን ፈሪዎች፣ የማያምኑ፣ ርኩሶች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝሮች፣ አስማተኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸተኞች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው በዲንና በእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይሆናል። ይህም ሁለተኛው ሞት ነው።”
ውሾች፣ አስማተኞች፣ ሴሰኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ ውሸትን የሚወድዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።