የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤ እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች።
ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት ከርሱ ጋራ መሬት ላይ ተቀመጡ፤ ሥቃዩ ታላቅ መሆኑንም ስለ ተረዱ፣ አንዳች ቃል የተናገረው አልነበረም።
ኢዮብም ገላውን ለማከክ ገል ወሰደ፤ በዐመድም ላይ ተቀመጠ።
በር ሆይ፤ ዋይ በል! ከተማ ሆይ፤ ጩኽ! ፍልስጥኤማውያን ሆይ፤ ሁላችሁም በፍርሀት ቅለጡ! ጢስ ከሰሜን መጥቶብሃል፤ ከሰልፉ ተነጥሎ የሚቀር የለምና።
ነገር ግን አርኤልን እከብባለሁ፤ ታለቅሳለች፤ ዋይ ዋይ ትላለች፤ ለእኔም እንደ መሠዊያ ስፍራ ትሆንልኛለች።
ዐምባ ምሽጉ ወና ይሆናል፤ ውካታ የበዛበት ከተማ ጭር ይላል፤ ምሽጉና ማማው ለዘላለሙ ዋሻ፣ የዱር አህያ መፈንጫ፣ የመንጋም መሰማሪያ ይሆናል፤
ምድሪቱ አለቀሰች፤ መነመነች፤ ሊባኖስ ዐፈረች፤ ጠወለገች፤ ሳሮን እንደ ዓረባ ምድረ በዳ ሆነች፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ።
“አንቺ የባቢሎን ድንግል ልጅ ሆይ፤ ውረጂ፤ በትቢያ ላይ ተቀመጪ፤ አንቺ የባቢሎናውያን ልጅ ሆይ፤ ከዙፋንሽ ውረጂ፤ መሬት ላይ ተቀመጪ፤ ከእንግዲህ ውብ ወይም ለግላጋ፣ ተብለሽ አትጠሪም።
እኔም፣ “ጌታ ሆይ፤ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” አልሁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፤ “ከተሞች እስኪፈራርሱና የሚኖሩባቸው እስኪያጡ፣ ቤቶችም ወና እስኪሆኑና ምድርም ፈጽሞ ባድማ እስክትሆን ድረስ፤
“ይሁዳ ታለቅሳለች፤ ከተሞቿም ይማቅቃሉ፤ በምድር ላይ ተቀምጠው ይቈዝማሉ፤ ጩኸትም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ይሰማል።
የመበለቶቻቸውን ቍጥር፣ ከባሕር አሸዋ ይልቅ አበዛለሁ፤ የጐበዛዝት እናቶች በሆኑትም ላይ፣ አጥፊውን በቀትር አመጣባቸዋለሁ። ሽብርንና ድንጋጤን፣ በድንገት አወርድባቸዋለሁ።
በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣ እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች! በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣ አሁን ባሪያ ሆናለች።
የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤ በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤ በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ ካህናቷ ይቃትታሉ፤ ደናግሏ ክፉኛ ዐዝነዋል፤ እርሷም በምሬት ትሠቃያለች።
የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች፣ በምድር ላይ በዝምታ ተቀምጠዋል፤ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤ ማቅም ለበሱ፤ የኢየሩሳሌም ወጣት ሴቶች፣ ራሳቸውን ወደ ምድር ዝቅ አደረጉ።
በጽዮን ሴት ልጅ ዙሪያ ያለውን ቅጥር፣ እግዚአብሔር ለማፍረስ ወሰነ፤ የመለኪያ ገመድ ዘረጋ፤ ከማጥፋትም እጆቹን አልሰበሰበም፤ ምሽጎችና ቅጥሮች እንዲያለቅሱ አደረገ፤ በአንድነትም ጠፉ።
ሰው ይኖርባቸው የነበሩ ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም ወና ትሆናለች። በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”
የባሕር ጠረፍ መሳፍንት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ይጥላሉ፤ ወርቀ ዘቦ ልብሳቸውን ያወልቃሉ። ፍርሀት ተከናንበው በመሬት ላይ በመቀመጥ ባለማቋረጥ፣ እየተንቀጠቀጡ በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ይሸበራሉ፤’
ቍስሏ የማይሽር ነውና፤ ለይሁዳ ተርፏል፤ እስከ ሕዝቤ መግቢያ በር፣ እስከ ኢየሩሳሌም እንኳ ደርሷል።
“ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም’
አንቺንና በቅጥርሽ ውስጥ የሚኖሩትንም ልጆችሽን ከዐፈር ይደባልቃሉ፤ ድንጋይም በድንጋይ ላይ አይተዉም፤ የመጐብኛሽን ጊዜ አላወቅሽምና።”