በአንተ ላይ ታምናለችና፣ በአንተ የምትደገፈውን ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ።
በጦርነቱም ላይ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው ስለ ነበር፣ በውጊያው ረዳቸው፤ አጋራውያንንና የጦር አጋሮቻቸውን ሁሉ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ስለ ታመኑበትም ጸሎታቸውን ሰማ።
በጦርነቱም የእስራኤል ሰዎች ተዋረዱ፣ የይሁዳ ሰዎች ግን በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነዋልና ድል ነሡ።
ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ቍጥር ካላቸው ሠረገላዎቻቸውና ፈረሶቻቸው ጋራ ኀያል ሰራዊት አልነበሩምን? ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ስለ ታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጠህ፤
ሕግህን የሚወድዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም።
በእግዚአብሔር የሚታመኑ፣ ሳትናወጥ ለዘላለም እንደምትኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው።
ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
እነሆ፣ አምላክ ድነቴ ነው፤ እታመናለሁ፣ ደግሞም አልፈራም፤ ጌታ እግዚአብሔር ብርታቴና ጋሻዬ ነው፤ ድነቴም ሆኗል።”
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰላምን መሠረትህልን፤ የሠራነውንም ሁሉ አንተ አከናወንህልን።
አለዚያ ይምጡና መሸሸጊያቸው ያድርጉኝ፤ ከእኔ ጋራ ሰላም ይፍጠሩ፤ አዎን፤ ከእኔ ጋራ ሰላም ያድርጉ።”
ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብጽ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው!
የጽድቅ ፍሬ ሰላም፣ የጽድቅ ውጤትም ጸጥታና ለዘላለም ያለ ሥጋት ይሆናል።
ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።
አገልጋዬ እንጂ፣ ሌላ ዕውር ማን አለ? ከምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ማን ደንቈሮ አለ? ለእኔ ታማኝ እንደ ሆነ ሰው የታወረ፣ እንደ እግዚአብሔርስ አገልጋይ ዕውር ማነው?
“እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ እጅህንም እይዛለሁ፤ እጠብቅሃለሁ፤ ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ።
እናንተ የቅድስቲቱ ከተማ ነዋሪዎች ነን ብላችሁ ራሳችሁን የምትጠሩ፣ በእስራኤል አምላክ የምትታመኑ፣ ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው የሚለውን አድምጡ፤
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በተወደደ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤ በድነት ቀን እረዳሃለሁ። ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣ እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እናታችሁን የፈታሁበት የፍች ወረቀት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥኋችሁ ለየትኛው አበዳሪዬ ነው? እነሆ፤ ስለ ኀጢአታችሁ ተሸጣችኋል፤ ስለ መተላለፋችሁም እናታችሁ ተፈትታለች።
ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው? ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣ ብርሃንም ከሌለው፣ በእግዚአብሔር ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ሰላምን እንደ ወንዝ ውሃ አፈስስላታለሁ፤ የመንግሥታትንም ብልጽግና እንደ ጅረት ውሃ አጐርፍላታለሁ፤ ትጠባላችሁ፤ በዕቅፏም ትያዛላችሁ፤ በጭኖቿም ላይ ትፈነድቃላችሁ።
እታደግሃለሁ፤ በእኔ ታምነሃልና በሕይወት ታመልጣለህ እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ”
ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።
ከዚያም ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፤ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና።
ንጉሡ እጅግ ተደስቶ፤ ዳንኤልን ከጕድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ነበርና ከጕድጓድ በወጣ ጊዜ፣ አንዳች ጕዳት አልተገኘበትም።
እርሱም ሰላማቸው ይሆናል። አሦራዊ ምድራችንን ሲወርር፣ ምሽጎቻችንንም ጥሶ ሲገባ፣ ሰባት እረኞችን፣ እንዲያውም ስምንት አለቆችን እናስነሣበታለን።
ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም።
“በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”
እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋራ ሰላም አለን።
ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።