እርሱ በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል። እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።
በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ በየአገሩ ያሉትንም ራሶች ከስክሶ ሬሳ በሬሳ ያደርጋቸዋል።
“ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ፤ በሕዝቦች ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።”
ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።
አምላክ ሆይ፤ ተነሥ፤ በምድር ላይ ፍረድ፣ ሕዝቦች ሁሉ ርስትህ ናቸውና።
እርሱ ይመጣልና በእግዚአብሔር ፊት ይዘምራሉ፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣል፤ በዓለም ላይ በጽድቅ፣ በሕዝቦችም ላይ በእውነት ይፈርዳል።
የጽድቅ ፍሬ ሰላም፣ የጽድቅ ውጤትም ጸጥታና ለዘላለም ያለ ሥጋት ይሆናል።
ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።
እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ የሚያድነንም እርሱ ነውና።
“እነሆ፤ ደግፌ የያዝሁት፣ በርሱም ደስ የሚለኝ የመረጥሁት አገልጋዬ፤ መንፈሴን በርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል።
የተቀጠቀጠ ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል።
የጦረኞች ጫማ ሁሉ፣ በደም የተለወሰ ልብስም ሁሉ፣ ለእሳት ይዳረጋል፤ ይማገዳልም።
ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም፣ መንግሥቱን በፍትሕና በጽድቅ ይመሠርታል፤ ደግፎ በመያዝም ያጸናዋል። በዳዊት ዙፋን ይቀመጣል፤ አገሩንም ሁሉ ይገዛል፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል።
በዚያ ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፣ በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ጋራ፣ ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ሁሉም ያለ ሥጋት እንዲኖሩ፣ ቀስትን፣ ሰይፍንና ጦርነትን፣ ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።
በታማኝነት ዐጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂያለሽ።”
ማረሻችሁ ሰይፍ፣ ማጭዳችሁም ጦር እንዲሆን ቀጥቅጡት፤ ደካማውም ሰው፣ “እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።
“ሕዝቦች ይነሡ፤ ወደ ኢዮሣፍጥም ሸለቆ ፈጥነው ይውረዱ፤ ዙሪያውን ባሉት ሕዝቦች ሁሉ ላይ ልፈርድ፣ በዚያ እቀመጣለሁና።
እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤ በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤ ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል። አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።
ሠረገሎችን ከኤፍሬም፣ የጦር ፈረሶችን ከኢየሩሳሌም እወስዳለሁ፤ የጦርነቱም ቀስት ይሰበራል፤ ሰላምን ለአሕዛብ ያውጃል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣ ከወንዙም እስከ ምድር ዳር ድረስ ይዘረጋል።
በመረጠው ሰው አማካይነት በዓለም ላይ በጽድቅ የሚፈርድበትን ቀን ወስኗልና፤ እርሱንም ከሙታን በማስነሣቱ ለሰዎች ሁሉ ይህን አረጋግጧል።”
ከዚያም ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆ አንድ ነጭ ፈረስ ነበረ፤ በፈረሱም ላይ፣ “ታማኝና እውነተኛ” የሚባል ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በጽድቅ ይፈርዳል፤ ይዋጋልም።
ከእግዚአብሔር ጋራ የሚጣሉ ይደቃሉ፤ እርሱ ከሰማይ ያንጐደጕድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል። “ለንጉሡ ኀይልን ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”