በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር አውራ መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራውያን ወደ ግብጽ፣ ግብጻውያንም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብጻውያንና አሦራውያን በአንድነት ያመልካሉ።
“ከሚያውቁኝ መካከል፣ ረዓብንና ባቢሎንን እጠቅሳለሁ፤ እነሆ፤ ፍልስጥኤምና ጢሮስ ከኢትዮጵያ ጋራ፣ ‘ይህ ሰው በዚያ ነው የተወለደው’ ይላሉ።”
በዚያ ቀን፣ ጌታ እጁን ዘርግቶ እንደ ገና የተረፈውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦር፣ ከግብጽ፣ ከጳትሮስ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኤላም፣ ከባቢሎን፣ ከሐማትና ከባሕር ጠረፍ ምድር ይሰበስባል።
እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ እንደ ሆነው ሁሉ፣ ከአሦር ለተረፈው ቅሬታ ሕዝብ፣ እንዲሁ ጐዳና ይዘጋጅለታል።
በዚያ ቀን እስራኤል፣ ከግብጽና ከአሦር ጋራ የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች።
ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ በጐዳናውም እንድንሄድ፤ መንገዱን ያስተምረናል።” ሕግ ከጽዮን፣ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
በዚያ ቀን ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦር የጠፉትና በግብጽ የተሰደዱትም መጥተው፣ በተቀደሰው ተራራ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያመልካሉ።
ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።
እግዚአብሔር፣ ታዳጊ የሆነው የእስራኤል ቅዱስ፣ ለተናቀውና በሕዝብ ለተጠላው፣ የገዦች አገልጋይ እንዲህ ይላል፤ “ነገሥታት አይተውህ ይነሣሉ፤ ልዑላንም አይተው ይሰግዳሉ፤ ምክንያቱም የመረጠህ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ታማኝ ነው።”
ዕለፉ፤ በበሮቹ በኩል ዕለፉ፤ ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤ አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ! ድንጋዩን አስወግዱ፤ ለመንግሥታትም ምልክት አሳዩ።
“ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤
በዚያ ቀን ሰዎች፣ ከአሦር እስከ ግብጽ ከተሞች፣ ከግብጽ እስከ ኤፍራጥስ፣ ከባሕር ወደ ባሕር፣ ከተራራ ወደ ተራራ ወደ እናንተ ይመጣሉ።