ሰማርያ ሆይ፤ የጥጃ ጣዖትሽን ጣዪ! ቍጣዬ በእነርሱ ላይ ነድዷል፤ የማይነጹት እስከ መቼ ነው?
“አሁንም እናንተ በዳዊት ዘርዐ ትውልድ እጅ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ዐስባችኋል። በርግጥም በሰራዊት ረገድ እጅግ ብዙ ናችሁ፤ አማልክታችሁ ይሆኑ ዘንድ ኢዮርብዓም የሠራቸውንም የወርቅ ጥጆች ይዛችኋል።
ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤ እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤ ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤ ከታላቅ በደልም እነጻለሁ።
“እናንተ አላዋቂዎች፤ ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወድዱታላችሁ? ፌዘኞች በፌዝ ደስ የሚሰኙት፣ ሞኞችስ ዕውቀትን የሚጠሉት እስከ መቼ ነው?
“በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤ እናንተ ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ። የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣ ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።
በኰረብቶችና በሜዳዎች ላይ፣ አስጸያፊ ተግባርሽን፣ ምንዝርናሽንና ማሽካካትሽን፣ ኀፍረተ ቢስ ግልሙትናሽን አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ወዮልሽ! ከርኩሰትሽ የማትጸጂው እስከ መቼ ነው?”
ኢየሩሳሌም ሆይ፤ እንድትድኚ ከልብሽ ክፋት ታጠቢ፤ እስከ መቼ ክፉ ሐሳብ በውስጥሽ ይኖራል?
የእስራኤል ቤት፤ በቤቴል ታምኖ እንዳፈረ ሁሉ፣ ሞዓብም በካሞሽ ያፍራል።
በሰማርያ የሚኖረው ሕዝብ፣ በቤትአዌን ስላለው የጥጃ ጣዖት ይፈራል፤ ሕዝቡም ያለቅስለታል፤ በክብሩ እጅግ ደስ ያላቸው ሁሉ፣ አመንዝራ ካህናትም እንደዚሁ ያለቅሱለታል፤ በምርኮ ከእነርሱ ተወስዷልና።
የእስራኤል ኀጢአት የሆነው፣ የአዌን ማምለኪያ ኰረብታ ይጠፋል፤ እሾኽና አሜከላ ይበቅልባቸዋል፤ መሠዊያዎቻቸውንም ይወርሳል፤ በዚያ ጊዜ ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ይላሉ።
አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የእጅ ጥበብ ባለሙያ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ!”
ይህም በእስራኤል ሆነ! የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራው ይህ ጥጃ፣ አምላክ አይደለም፤ ያ የሰማርያ ጥጃ፣ ተሰባብሮ ይደቅቃል።
በሰማርያ በደል የሚምሉ፣ ወይም፣ ‘ዳን ሆይ፤ ሕያው አምላክህን’ የሚሉ፣ ወይም ‘ሕያው የቤርሳቤህ አምላክን’ ብለው የሚምሉ፣ ዳግመኛ ላይነሡ፣ ለዘላለም ይወድቃሉ።”
ጣዖቶቿ ሁሉ ይሰባበራሉ፤ ለቤተ መቅደሷ የቀረበው ገጸ በረከት በእሳት ይቃጠላል፤ ምስሎቿን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ ገጸ በረከቷን በዝሙት ዐዳሪነት እንደ ሰበሰበች ሁሉ፣ አሁንም ገጸ በረከቷ የዝሙት ዐዳሪነት ዋጋ መቀበያ ይሆናል።”
በዚያ ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም።
በቍጣዬ እሳት ተቀጣጥሏልና፤ እርሱ እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነድዳል። ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤ የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል።