አሦር ሊያድነን አይችልም፤ በጦር ፈረሶችም ላይ አንቀመጥም፤ ከእንግዲህም የገዛ እጆቻችን የሠሯቸውን፣ ‘አምላኮቻችን’ አንላቸውም፤ ድኻ አደጉ ከአንተ ርኅራኄ ያገኛልና።”
በዚያ ጊዜም ባለራእዩ አናኒ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ሳይሆን በሶርያ ንጉሥ ስለ ታመንህ፣ የሶርያ ንጉሥ ሰራዊት ከእጅህ አምልጧል።
አንተ ግን መከራንና ሐዘንን ታያለህ፤ በእጅህም ዋጋ ለመክፈል ትመለከታለህ፤ ምስኪኑም ራሱን በአንተ ላይ ይጥላል፤ ለድኻ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።
በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችም አትመኩ።
እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድኻ አደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
በፈረስ ድል አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ተስፋ ነው፤ በብርቱ ጕልበቱም ማንንም አያድንም።
እግዚአብሔር በተቀደሰ ማደሪያው፣ ለድኻ አደጉ አባት፣ ለባልቴቲቱም ተሟጋች ነው።
“ደስ በተሰኛችሁባቸው የአድባር ዛፎች ታፍራላችሁ፤ በመረጣችኋቸውም የአትክልት ቦታዎች ትዋረዳላችሁ።
በዚያ ቀን ሰዎች ሊያመልኳቸው ያበጇቸውን፣ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይወረውራሉ።
ያዕቆብ የመሠዊያ ድንጋዮችን፣ እንደ ኖራ ድንጋይ ፈጭቶ ሲያደቅቃቸው፣ የአሼራን ዐምድና የዕጣን መሠዊያዎችን፣ ከቦታቸው ነቅሎ ሲጥል፣ በዚያ ጊዜ በደሉ ይሰረይለታል፤ ይህም ኀጢአቱ የመወገዱ ሙሉ ፍሬ ይሆናል።
ደግሞም ‘አይሆንም፣ በፈረስ እንሸሻለን’ አላችሁ፤ ስለዚህ ትሸሻላችሁ! ደግሞም፣ ‘በፈጣን ፈረስ እናመልጣለን’ አላችሁ፤ ስለዚህ አሳዳጆቻችሁም ፈጣን ይሆናሉ።
እኔን ሳይጠይቁ፣ ወደ ግብጽ ይወርዳሉ፤ የፈርዖንን ከለላ፣ የግብጽንም ጥላ ለመጠጊያነት ይፈልጋሉ።
ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብጽ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው!
ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን ሲዘረጋ፣ ርዳታ ሰጪው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።
“ ‘አሁን ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋራ ተደራደር፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ!
ወላጆች የሌላቸውን ልጆችህን ተዋቸው፤ እኔ ለሕይወታቸው እጠነቀቃለሁ፤ መበለቶቻችሁም በእኔ ይታመኑ።”
ንጹሕ ውሃ እረጫችኋለሁ፤ እናንተም ንጹሕ ትሆናላችሁ፤ ከርኩሰታችሁ ሁሉና ከጣዖታቶቻችሁ ሁሉ አነጻችኋለሁ።
በጣዖቶቻቸው፣ በአስጸያፊ ምስሎቻቸው ወይም በማንኛውም ኀጢአት ራሳቸውን አያረክሱም፤ ነገር ግን እኔን በመተው ከሠሩት ኀጢአት ሁሉ አድናቸዋለሁ፤ አነጻቸዋለሁም። እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ።
ኤፍሬም የነፋስ እረኛ ነው፤ ቀኑን ሙሉ የምሥራቅን ነፋስ ይከተላል፤ ሐሰትንና ዐመፅን ያበዛል። ከአሦር ጋራ ቃል ኪዳን ያደርጋል፤ የወይራ ዘይትንም ወደ ግብጽ ይልካል።
አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የእጅ ጥበብ ባለሙያ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሏል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ!”
ኤፍሬም ሆይ፤ ከእንግዲህ ከጣዖት ጋራ ምን ጕዳይ አለኝ? የምሰማህና የምጠነቀቅልህ እኔ ነኝ፤ እኔ እንደ ለመለመ የጥድ ዛፍ ነኝ፤ ፍሬያማነትህም ከእኔ የተነሣ ነው።”
የበኣል አማልክትን ስም ከአንደበቷ አስወግዳለሁ፤ ከእንግዲህም ስሞቻቸው አይነሡም።
ከዕንጨት የተሠራውን ጣዖት ምክር ይጠይቃሉ፤ ዘንጋቸውም ይመልስላቸዋል። የአመንዝራነት መንፈስ ያስታቸዋል፤ ለአምላካቸውም ታማኝ አልሆኑም።
“ኤፍሬም ሕመሙን፣ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ፣ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ፤ ርዳታ ለመጠየቅ ወደ ታላቁ ንጉሥ መልእክተኛ ላከ፤ እርሱ ግን ሊያድናችሁ፣ ቍስላችሁንም ሊፈውስ አይችልም።
“ኤፍሬም በቀላሉ እንደምትታለል፣ አእምሮም እንደሌላት ርግብ ነው፤ አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አሦር ይዞራል።
ይህም በእስራኤል ሆነ! የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራው ይህ ጥጃ፣ አምላክ አይደለም፤ ያ የሰማርያ ጥጃ፣ ተሰባብሮ ይደቅቃል።
ለብቻው እንደሚባዝን የዱር አህያ፣ ወደ አሦር ሄደዋልና፤ ኤፍሬም በእጅ መንሻ ወዳጅ አበጀ።
እግዚአብሔርም ዓሣውን አዘዘው፤ ዮናስንም በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።
“በዚያ ቀን የጣዖታትን ስም ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም አይታሰቡም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ነቢያትንና ርኩስ መንፈስን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።
ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።
ንጉሡም ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ፤ ወይም ደግሞ የፈረሰኞችን ቍጥር ለመጨመር ሕዝቡን ወደ ግብጽ አይመልስ፤ እግዚአብሔር፣ “በዚያ መንገድ ፈጽሞ አትመለሱ” ብሏችኋልና።