እንደ ወፍ ከግብጽ፣ እንደ ርግብ ከአሦር፣ እየበረሩ ይመጣሉ፤ እኔም በቤታቸው አኖራቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
በዚያ ቀን፣ ጌታ እጁን ዘርግቶ እንደ ገና የተረፈውን የሕዝቡን ቅሬታ ከአሦር፣ ከግብጽ፣ ከጳትሮስ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኤላም፣ ከባቢሎን፣ ከሐማትና ከባሕር ጠረፍ ምድር ይሰበስባል።
“ርግቦች ወደ ጐጇቸው እንደሚበርሩ፣ እንደ ደመና የሚጓዙ እነዚህ እነማን ናቸው?
መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣ በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣ በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህም አያዝኑም።
የየሜዳው ዛፍ ፍሬ ይሰጣል፤ መሬቱም እህል ያበቅላል። ሕዝቡም በምድሪቱ ላይ ያለ ሥጋት ይኖራሉ። የቀንበሮቻቸውን ማነቆ ሰብሬ በባርነት ከገዟቸው እጅ ሳድናቸው፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
ከእንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ንጥቂያ አይዳረጉም፤ የዱር አራዊት አይቦጫጭቋቸውም፤ ያለ ሥጋት ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።
እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል።
ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በመጨረሻውም ዘመን በመንቀጥቀጥ ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።
“ኤፍሬም በቀላሉ እንደምትታለል፣ አእምሮም እንደሌላት ርግብ ነው፤ አንድ ጊዜ ወደ ግብጽ ይጣራል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ አሦር ይዞራል።
ነገር ግን በጽዮን ተራራ ነጻ መውጣት ይሆናል፤ የያዕቆብ ቤትም እርሷ የተቀደሰች ትሆናለች፤ ርስታቸውን ይወርሳሉ።
ከግብጽ እመልሳቸዋለሁ፤ ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ አመጣቸዋለሁ፤ በቂ ስፍራም አይገኝላቸውም።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋለሁ።
በኢየሩሳሌም እንዲኖሩ መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም በጽድቅና በታማኝነት አምላካቸው እሆናለሁ።”