ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።
አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም እግዚአብሔር የዘላለም አምላክን ስም ጠራ።
የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤
ገና ተራሮች ሳይወለዱ፣ ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ በፊት፣ አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ።
ሺሕ ዓመት በፊትህ፣ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣ እንደ ሌሊትም እርቦ ነውና።
እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እኔ፣ ያለሁና የምኖር ነኝ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ልኮኛል’ ብለህ ንገራቸው” አለው።
ይህን የሠራና ያደረገ፣ ትውልድን ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር ከፊተኛው፣ ከኋለኛውም ጋራ፤ እኔው ነኝ።”
“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
“እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም።
ምክንያቱም እኔም ሆንሁ ሲላስና ጢሞቴዎስ፣ እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አዎን” እና “አይደለም” አልነበረም፤ ነገር ግን በርሱ ዘወትር፣ “አዎን” ነው።
በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ “አዎን” የሚሆኑት በርሱ ነውና፤ እኛም በርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ “አሜን” የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።
እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤ እንደ ልብስም ይለወጣሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።”
በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም።
እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለምም ድረስ ክብር፣ ግርማ፣ ኀይልና ሥልጣን ይሁን! አሜን።
ድምፁም፣ “የምታየውን በጥቅልል መጽሐፍ ጽፈህ በኤፌሶን፣ በሰምርኔስ፣ በጴርጋሞን፣ በትያጥሮን፣ በሰርዴስ፣ በፊላድልፍያና በሎዶቅያ ወደሚገኙት ወደ ሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት ላክ” አለ።
ከዮሐንስ፤ በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው፣ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፣
“ያለውና የነበረው፣ የሚመጣውም፣ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ፣ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ” ይላል።