“በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን ለሚገነባ፣ ከጠላት እጅ ለማምለጥ፣ ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት!
መሬቶችን በስማቸው ቢሰይሙም፣ መቃብራቸው የዘላለም ቤታቸው፣ ከትውልድ እስከ ትውልድም መኖሪያቸው ይሆናል።
“እግዚአብሔርን መጠጊያ ያላደረገ፣ ነገር ግን በሀብቱ ብዛት የተመካ፣ በክፋቱም የበረታ፣ ያ ሰው እነሆ!”
እናንተ፣ “ከሞት ጋራ ቃል ኪዳን ገብተናል፤ ከሲኦልም ጋራ ስምምነት አድርገናል፤ ውሸትን መጠጊያችን፣ ሐሰትን መደበቂያችን አድርገናል፤ ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ ሊነካን አይችልም” በማለት ታብያችኋል።
ስፍራ ለሌሎች እስከማይተርፍ፣ ቤትን በቤት ላይ በመጨመር፣ መሬትን ከመሬት ጋራ በማያያዝ፣ ለብቻችሁ በምድር ተስፋፍታችሁ ለምትኖሩ ወዮላችሁ!
ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣ ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤ በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤ በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል።
አንቺ፣ ‘በሊባኖስ’ ውስጥ የምትኖሪ፣ መኖሪያሽን በዝግባ ዛፍ የሠራሽ ሆይ፤ ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣ መከራ በላይሽ ሲመጣ ጩኸትሽ እንዴት ይሆን!
አንተ በዐለት ንቃቃት ውስጥ የምትኖር፣ የተራራውንም ከፍታ የያዝህ ሆይ፤ የምትነዛው ሽብር፣ የልብህም ኵራት አታልሎሃል፤ መኖሪያህን እስከ ንስር ከፍታ ቦታ ብትሠራም፣ ከዚያ ወደ ታች አወርድሃለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
አንቺ በብዙ ውሃ አጠገብ የምትኖሪ፣ በሀብትም የበለጸግሽ ሆይ፤ የምትወገጂበት ጊዜ ወጥቷል፤ ፍጻሜሽ ደርሷል።
ባቢሎን ወደ ሰማይ ብትወጣም፣ ከፍ ያለ ምሽጓን ብታጠናክርም፣ አጥፊዎች እሰድድባታለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈስሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ።
እንደ ንስር መጥቀህ ወደ ላይ ብትወጣ፣ ጐጆህንም በከዋክብት መካከል ብታደርግ፣ ከዚያ ወደ ታች አወርድሃለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
ወዮላቸው! በቃየን መንገድ ሄደዋል፤ ለገንዘብ ሲስገበገቡ በበለዓም ስሕተት ውስጥ ወድቀዋል፤ በቆሬም ዐመፅ ጠፍተዋል።