ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣ ገዥ እንደሌላቸውም እንደሚርመሰመሱ ፍጥረታት አደረግህ።
አዛዥ የለውም፤ አለቃም ሆነ ገዥ የለውም፤
“አሁን ግን ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እነርሱም ያጠምዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ ዐዳኞችን እሰድዳለሁ፤ እነርሱም ከየተራራው፣ ከየኰረብታው ሁሉ ከየዐለቱም ስንጣቂ ዐድነው ይይዟቸዋል።
ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤ አንተ በደልን መመልከት አትችልም፤ ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትመለከታለህ? ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣ ለምን ዝም ትላለህ?
ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤ በመረቡ ይይዛቸዋል፤ በወጥመዱ ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤ በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል።