ከዚያም ያ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ መልሶ አመጣኝ፤ ከቤተ መቅደሱ መድረክ ሥር ውሃ እየወጣ፣ ወደ ምሥራቅ ይፈስስ ነበር፤ ቤተ መቅደሱ ለምሥራቅ ትይዩ ነበርና። ውሃው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል፣ በመሠዊያው ደቡብ በኩል፣ ሥር ሥሩን ይወርዳል።
የእግዚአብሔርን ከተማ፣ የልዑልን የተቀደሰ ማደሪያ ደስ የሚያሰኙ የወንዝ ፈሳሾች አሉ።
እግዚአብሔር በመካከሏ ነው፤ አትናወጥም፤ አምላክ በማለዳ ይረዳታል።
የሚያዜሙም መሣሪያ የሚጫወቱም፣ “ምንጩ ሁሉ በአንቺ ውስጥ ይገኛል” ይላሉ።
ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ በጐዳናውም እንድንሄድ፤ መንገዱን ያስተምረናል።” ሕግ ከጽዮን፣ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።
በታላቁ የዕልቂት ቀን ምሽጎች ሲፈርሱ፣ በረጅም ተራራ ሁሉና ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ላይ ወራጅ ወንዝ ይፈስሳል።
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንተ ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም! ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።
“ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል፤ ሕያው የውሃ ምንጭ የሆንሁትን፣ እኔን ትተዋል፤ ውሃ መያዝ የማይችሉትን ቀዳዳ የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓዶች፣ ለራሳቸው ቈፍረዋል።
ከዚያም በምሥራቅ ትይዩ ወዳለው በር መጣ፤ ደረጃዎቹን ወጥቶ የበሩን መግቢያ መድረክ ለካ፤ ቁመቱም አንድ ዘንግ ነበር።
የመግቢያውም በር ወርድ ዐሥር ክንድ ሲሆን፣ በግራና በቀኝ በኩል ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ወርድ ዐምስት ክንድ ነበር። ደግሞም የውስጡን መቅደስ ለካ፤ ርዝመቱ አርባ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ክንድ ነበር።
እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ፣ በቤተ መቅደሱ የሚያገለግሉቱ፣ የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው።”
በወንዙም ዳርና ዳር፣ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶች ሁሉ ይበቅላሉ፤ ቅጠላቸው አይደርቅም፤ ፍሬ አልባም አይሆኑም። ከመቅደሱ የሚወጣው ውሃ ስለሚፈስላቸው በየወሩ ያፈራሉ፤ ፍሬአቸው ለምግብ፣ ቅጠላቸውም ለፈውስ ይሆናል።”
ከዚያም በሰሜኑ በር በማውጣት በውጭ አዙሮ በምሥራቅ አቅጣጫ ወዳለው የውጭ በር መራኝ፤ ውሃውም በደቡብ በኩል ይፈስስ ነበር።
“በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤ ኰረብቶችም ወተት ያፈስሳሉ፤ በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎች ሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔር ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤ የሰጢምን ሸለቆ ያጠጣል።
“በዚያ ቀን የዳዊትን ቤትና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከኀጢአትና ከርኩሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።
በዚያ ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤
በዚያ ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።
ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ መስተዋት የጠራውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤
መንፈስና ሙሽራዪቱ፣ “ና” ይላሉ፤ የሚሰማም፣ “ና” ይበል፤ የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነጻ ይውሰድ።