ይሁን እንጂ ገዥው ከርስቱ ላይ ከባሪያዎቹ ለአንዱ ቢሰጥ፣ ባሪያው ነጻ እስከሚወጣበት ዓመት ድረስ የራሱ ሊያደርገው ይችላል፤ ከዚያም ርስቱ ለገዢው ይመለስለታል፤ ርስቱም ለወንድ ልጆቹ ብቻ የሚተላለፍ ይሆናል፤ የእነርሱም ነው።
ገዥው ከንብረታቸው በማፈናቀል፤ የትኛውንም የሕዝቡን ርስት መውሰድ አይገባውም፤ ለወንድ ልጆቹ ርስት መስጠት ያለበት ከራሱ ንብረት ነው፤ ይኸውም ከሕዝቤ ማንም ከርስቱ እንዳይነቀል ነው።’ ”
ዐምሳኛውን ዓመት ቀድሱ፤ በምድሪቱ ሁሉ ላሉ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነት ዐውጁ፤ ይህም ኢዮቤልዩ ይሁንላችሁ፤ ከእናንተ እያንዳንዱ ወደ ቤተ ሰቡ ርስት፣ ወደ ወገኑም ይመለስ።