በደቡብ በኩል የውጩን አደባባይ ግንብ ተከትሎ፣ ከቤተ መቅደሱ አደባባይ ጋራ የተያያዙና ከውጩ ግንብ ጋራ ትይዩ የሆኑ ክፍሎች አሉ፤
ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ እዚያም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ክፍሎችና ድንጋይ የተነጠፈበት መመላለሻ አየሁ፤ በመመላለሻውም ዙሪያ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።
ከዚያም ያ ሰው በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ውጩ አደባባይ በማምጣት፣ በቤተ መቅደሱ አደባባይ ትይዩና በሰሜን በኩል ባለው ግንብ ትይዩ ወደ አሉት ክፍሎች አመጣኝ።
ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ከቤተ መቅደሱ አደባባይ ፊት ለፊት ያሉት የሰሜኑና የደቡቡ ክፍሎች የካህናቱ ሲሆኑ፣ እነዚህም በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡት ካህናት እጅግ የተቀደሱትን ቍርባኖች የሚበሉባቸው ናቸው። በዚያም እጅግ የተቀደሱትን ቍርባኖች ማለት የእህሉን ቍርባን፣ የኀጢአቱን ቍርባን፣ የበደሉን ቍርባን ያስቀምጣሉ፤ ቦታው ቅዱስ ነውና።
ከክፍሎቹና፣ ከውጩ አደባባይ ትይዩ የሆነ የውጪ ግንብ አለ፤ ይህም በክፍሎቹ ፊት ለፊት ሆኖ ዐምሳ ክንድ ይረዝማል።