ከዚያም የቤተ መቅደሱን ግንብ ለካ፤ ውፍረቱ ስድስት ክንድ ነው፤ በቤተ መቅደሱ ግንብ ዙሪያ ግራና ቀኝ ያለው የእያንዳንዱ ክፍል ወርድ አራት ክንድ ነበር።
ከክፍቱ ቦታ ግራና ቀኝ ወዳሉ ክፍሎች የሚያስገቡ በሮች ነበሩ። አንዱ በሰሜን በኩል ሲሆን፣ ሌላው በር ደግሞ በደቡብ በኩል ነው። ክፍቱን ቦታ ዙሪያውን የሚያገናኘው መሠረት ስፋቱ ዐምስት ክንድ ነው።
በመተላለፊያ በረንዳውም ግራና ቀኝ ግንብ ላይ የዘንባባ ዛፍ ቅርጽ ያለባቸው ጠባብ መስኮቶች ነበሩ። ግራና ቀኝ ያሉት ክፍሎችም በደረጃው በኩል የሚሸፍን ጣራ ነበራቸው።