እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር።
ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ መራኝ፤ እዚያም ፊቱን ወደ ደቡብ ያደረገ በር አየሁ፤ እርሱም የውስጠኛውን ግድግዳና መተላለፊያ በረንዳውን ለካ፤ የእነዚህም መጠን እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።
የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋራ ተመሳሳይ ነበር፤ መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳዎቹ ዙሪያቸውን መስኮቶች ነበሯቸው፤ ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ ዐምስት ክንድ ነበር።
መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጿል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።