ከዚያም ከታችኛው መግቢያ በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት አንድ መቶ ክንድ ነበር።
የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋራ ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።
ልክ በምሥራቅ በኩል እንዳለው ሁሉ፣ ከሰሜኑ በር ጋራ ትይዩ የሆነ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያመራ በር አለ። ከአንዱ በር እስከ ሌላው በር ያለውን ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ነበር።
ውስጠኛው አደባባይ ደግሞ ከደቡብ ጋራ ትይዩ የሆነ በር አለው፤ እርሱም ከዚህ በር አንሥቶ በደቡብ አቅጣጫ እስካለው እስከ ውጭው በር ድረስ ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ሆነ።
ከዚያም አደባባዩን ለካው፤ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ፣ ወርዱ መቶ ክንድ እኩል በእኩል ባለአራት ማእዘን ነበር። መሠዊያውም በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ነበር።