ከእነርሱም ጋራ የሰላም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ቃል ኪዳኑም የዘላለም ይሆናል። አጸናቸዋለሁ፤ አበዛቸዋለሁ፤ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘላለም አኖራለሁ።
በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋራ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ እሆናለሁ።
ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእግዚአብሔርና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን ዐስባለሁ።”
“የእኔስ ቤት በአምላክ ዘንድ ትክክል አይደለምን? ሁሉንም ነገር አዘጋጅቶና ጠብቆ፣ ከእኔ ጋራ ዘላለማዊ ኪዳን ያደረገ አይደለምን? ድነቴን ከፍጻሜ የሚያደርሰው፣ መሻቴን ሁሉ የሚሰጠኝ እርሱ አይደለምን?
ወደ ላይ ዐረግህ፤ ምርኮ አጋበስህ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ አንተ በዚያ ትኖር ዘንድ፣ ከዐመፀኞችም ሳይቀር፣ ከሰዎች ስጦታን ተቀበልህ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ማደሪያህ እንዲሆን በሠራኸው ስፍራ፣ ጌታ ሆይ፤ እጆችህ በሠሩት መቅደስ፣ በርስትህ ተራራ ላይ፣ ታመጣቸዋለህ፤ ትተክላቸዋለህም።
“ከዚያም መቅደስ እንዲሠሩልኝ አድርግ፤ እኔም በመካከላቸው ዐድራለሁ።
በሚመጡት ቀናት ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፤ እስራኤልም ያቈጠቍጣል፣ ያብባልም፤ በፍሬአቸውም ምድርን ሁሉ ይሞላሉ።
በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣ ‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው? እኔ ሐዘንተኛና መካን፣ የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤ እነዚህን ማን አሳደጋቸው? ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’ ”
ጆሯችሁን ከፍታችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤ ነፍሳችሁም እንድትኖር አድምጡኝ። ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።
ከእነርሱም የምስጋና መዝሙር፣ የእልልታ ድምፅ ይሰማል። እኔ አበዛቸዋለሁ፤ ቍጥራቸውም አይቀንስም፣ አከብራቸዋለሁ፤ የተናቁም አይሆኑም።
“እነሆ፤ የእስራኤልን ቤትና የይሁዳን ቤት” ይላል እግዚአብሔር፤ “በሰውና በእንስሳት ዘር የምሞላበት ጊዜ ይመጣል፤
“ከእስራኤል ቤትና፣ ከይሁዳ ቤት ጋራ” ይላል እግዚአብሔር፣ “አዲስ ኪዳን የምገባበት፣ ጊዜ ይመጣል።
መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋራ የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።
“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በአሕዛብ መካከል ብሰድዳቸውም፤ በአገሮች መካከል ብበታትናቸውም፣ በሄዱባቸው አገሮች ሁሉ ለጥቂት ጊዜ መቅደስ ሆኛቸዋለሁ።’
ነገር ግን በልጅነትሽ ጊዜ ከአንቺ ጋራ የገባሁትን ቃል ኪዳን ዐስባለሁ፤ ለዘላለምም የሚኖር ቃል ኪዳን ከአንቺ ጋራ እመሠርታለሁ።
ስለዚህ ከአንቺ ጋራ ቃል ኪዳኔን ዐድሳለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ።
ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋራ አጣብቃችኋለሁ።
በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋራ በዚያ እሻለሁ።
“ ‘ከእነርሱ ጋራ የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚያም ምድሪቱን ከዱር አራዊት ነጻ አደርጋለሁ፤ እነርሱም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በደንም ውስጥ ያለ ሥጋት ይተኛሉ።
መላው የእስራኤል ቤት እንኳ ሳትቀሩ፣ የሰዎችን ቍጥር በእናንተ ላይ አበዛለሁ። ከተሞች የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈረሱት እንደ ገና ይሠራሉ።
በእናንተ ላይ የሰዎችንና የእንስሳትን ቍጥር እጨምራለሁ፤ ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ቍጥራቸውም ይበዛል። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሰዎች በውስጣችሁ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ካለፈው የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደ ገና ለእስራኤል ቤት ልመና ዕሺ እላለሁ፤ ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ ሕዝባቸውን እንደ በግ መንጋ አበዛዋለሁ፤
እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ የእግሬም ጫማ ማሳረፊያ ነው፤ በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም የምኖርበትም ስፍራ ነው። የእስራኤል ቤትም ሆኑ ነገሥታታቸው በአመንዝራነታቸውና በማምለኪያ ኰረብታቸው ላይ በሚያመልኳቸው፣ ሕይወት በሌላቸው በነገሥታታቸው ጣዖታት ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።
ከእንግዲህ አመንዝራነታቸውንና ሕይወት የሌላቸውን የንጉሦቻቸውን ጣዖታት ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።
“የከተማዪቱም ዙሪያ ዐሥራ ስምንት ሺሕ ክንድ ይሆናል፤ “የከተማዪቱ ስም፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ” ይሆናል።
እግዚአብሔር ቅጣትሽን አስወግዶታል፤ ጠላቶችሽን ከአንቺ መልሷል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲያ አንዳች ክፉ ነገር አትፈሪም።
እኔ ራሴ በዙሪያዋ የእሳት ቅጥር እሆንላታለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፣ ‘በውስጧም ክብሯ እሆናለሁ።’
ስለዚህ እነሆ እኔ የሰላም ቃል ኪዳኔን ከርሱ ጋራ እንደማደርግ ንገረው።
ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም።
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋራ ምን ስምምነት አለው? እኛ እኮ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ “ከእነርሱ ጋራ እኖራለሁ፤ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”
እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።”