“ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጕብታ ላይ ትሠራለች፤ ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል።
እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”
እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዕውሮችና ዐንካሶች፣ ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤ ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።
‘በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ ያለ ሥጋትም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።
“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።’
ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።
ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሕዝቤ ሆይ፤ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤ ከውስጣቸው አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር መልሼ አመጣችኋለሁ።
እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው አሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየስፍራው ሰብስቤ ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
አባቶቻችሁ በኖሩበት፣ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠሁት ምድር ይኖራሉ። በዚያም እነርሱ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘላለም ይኖራሉ፤ ባሪያዬ ዳዊትም ለዘላለም ንጉሣቸው ይሆናል።
ከብዙ ቀን በኋላ ለጦርነት ትጠራለህ። በኋለኛው ዘመንም ከጦርነት ያገገመችውን፣ ሕዝቧ ከአያሌ አሕዛብ መካከል ወጥቶ የተሰበሰበውን፣ ለብዙ ጊዜ ባድማ በነበረው በእስራኤል ተራሮች ላይ የሰፈረውን ወገን ትወርራለህ። ከሕዝቦች መካከል ወጥተው፣ አሁን ሁሉም ያለ ሥጋት ይኖራሉ።
የይሁዳ ሕዝብና የእስራኤል ሕዝብ እንደ ገና አንድ ይሆናሉ፤ አንድ መሪም ይሾማሉ፤ አንድ ሆነውም በምድሪቱ ይገንናሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።