ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።
አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እናቀርብ ዘንድ፣ አንተን በመወደስ እንጓደድ ዘንድ፣ ከአሕዛብም መካከል ሰብስበህ አምጣን።
በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ።
በታላቁ የዕልቂት ቀን ምሽጎች ሲፈርሱ፣ በረጅም ተራራ ሁሉና ከፍ ባለውም ኰረብታ ሁሉ ላይ ወራጅ ወንዝ ይፈስሳል።
የተማረኩትን፣ ‘ኑ ውጡ’ በጨለማ ያሉትን፣ ‘ነጻ ሁኑ!’ እንድትል አድርጌሃለሁ። “በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤ በተራቈተውም ኰረብታ ሁሉ ላይ መሰማሪያ ያገኛሉ።
ነገር ግን፣ ‘እስራኤልን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ይላሉ፤ ከዚያ በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።”
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጕብታ ላይ ትሠራለች፤ ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል።
እነሆ፣ ሕዝቤን እስራኤልንና ይሁዳን’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር የምመልስበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እነርሱም ይወርሷታል’ ይላል እግዚአብሔር።”
እነሆ፤ ከሰሜን ምድር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፤ በመካከላቸውም ዕውሮችና ዐንካሶች፣ ነፍሰ ጡርና በምጥ ላይ ያሉ ሴቶች ይገኛሉ፤ ታላቅም ሕዝብ ሆነው ይመለሳሉ።
‘በጽኑ ቍጣዬና በታላቅ መቅሠፍቴ እነርሱን ካሳደድሁበት ምድር ሁሉ በእውነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ ያለ ሥጋትም እንዲቀመጡ አደርጋቸዋለሁ።
“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰውም ሆነ እንስሳት በማይኖሩበት በዚህ ባዶ ስፍራ፣ በከተማዎቹም ሁሉ እረኞች መንጎቻቸውን የሚያሳርፉበት እንደ ገና ያገኛሉ።
እስራኤልንም ወደ መሰማሪያው እመልሰዋለሁ፤ በቀርሜሎስና በባሳን ላይ ይሰማራል፤ በኤፍሬም ተራሮችና በገለዓድም ላይ፣ እስኪጠግብ ይመገባል።
“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።’
ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።
ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ሰዎችን፣ ሕዝቤን እስራኤልን በእናንተ ላይ እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ ይወርሷችኋል፤ እናንተም ርስታቸው ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።
“ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ።
ከርኩሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም።
ከራብ የተነሣ በአሕዛብ መካከል በውርደት እንዳትሳቀቁ፣ የዛፉን ፍሬና የዕርሻውን ሰብል አበዛለሁ።
ከብዙ ቀን በኋላ ለጦርነት ትጠራለህ። በኋለኛው ዘመንም ከጦርነት ያገገመችውን፣ ሕዝቧ ከአያሌ አሕዛብ መካከል ወጥቶ የተሰበሰበውን፣ ለብዙ ጊዜ ባድማ በነበረው በእስራኤል ተራሮች ላይ የሰፈረውን ወገን ትወርራለህ። ከሕዝቦች መካከል ወጥተው፣ አሁን ሁሉም ያለ ሥጋት ይኖራሉ።
“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
ከአሕዛብ ምድር መልሼ ሳመጣቸው፣ ከጠላቶቻቸው አገር ስሰበስባቸው የራሴን ቅድስና በእነርሱ በኩል በብዙ ሕዝቦች ፊት አሳያለሁ።
የተሰደደውን ሕዝቤን እስራኤልን እመልሳለሁ። “እነርሱም የፈራረሱትን ከተሞች መልሰው ሠርተው በውስጣቸው ይኖራሉ። የወይን ተክል ተክለው፣ ጠጁን ይጠጣሉ፤ አትክልት ተክለው ፍሬውን ይበላሉ።
“ያዕቆብ ሆይ፤ በርግጥ ሁላችሁንም እሰበስባለሁ፤ የእስራኤልንም ትሩፍ በአንድነት አመጣለሁ፤ በጕረኖ ውስጥ እንዳሉ በጎች በመሰማሪያ ላይ እንዳለ መንጋ በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ፤ ቦታውም በሕዝብ ይሞላል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤ ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣ ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።
በእግዚአብሔር ኀይል፣ በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ታላቅነት፣ ጸንቶ ይቆማል፤ መንጋውንም ይጠብቃል። በዚያ ጊዜ ኀያልነቱ እስከ ምድር ዳርቻ ስለሚደርስ፣ ተደላድለው ይኖራሉ።
የእስራኤል ቅሬታዎች ኀጢአት አይሠሩም፤ ሐሰትም አይናገሩም፤ በአንደበታቸውም ተንኰል አይገኝም። ይበላሉ፤ ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።”
አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል።