“የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አስቸጋሪ በሆነ ዘመቻ ሰራዊቱን በጢሮስ ላይ አንቀሳቀሰ፤ የሁሉም ራስ ተመልጧል፤ የሁሉም ትከሻ ተልጧል፤ ይሁን እንጂ እርሱና ሰራዊቱ በጢሮስ ላይ ካደረጉት ዘመቻ ያተረፉት ነገር የለም።
የሰሜንን ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ሰዎች የሚጸየፏቸውና የሚሣለቁባቸው፣ የዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ፤
አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ የዱር አራዊት እንኳ እንዲገዙለት አደርጋለሁ።
የእያንዳንዱ ሰው ራስ፣ ጢምም ሁሉ ተላጭቷል፤ እጅ ሁሉ ተቸፍችፏል፤ ወገብም ሁሉ ማቅ ታጥቋል።
ስለ አንቺ ጠጕራቸውን ይላጫሉ፤ ማቅም ይለብሳሉ፤ በነፍስ ምሬት፣ በመራራም ሐዘን ያለቅሱልሻል።