በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?
ይህም ሆኖ እግዚአብሔር፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ አባቶቻችሁ እንዲፈጽሙት ባዘዝኋቸው ሕግ ሁሉ መሠረት እንዲሁም በአገልጋዮቼ በነቢያት አማካይነት ለእናንተ ባስተላለፍሁት ሕግ መሠረት፣ ትእዛዜንና ሥርዐቴን ጠብቁ” ብሎ በነቢያቱና በባለራእዮች ሁሉ እስራኤልንና ይሁዳን አስጠንቅቆ ነበር።
ከክፉ ሽሽ፤ መልካሙንም አድርግ፤ ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም።
አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
የሚያጣኝ ሁሉ ግን ራሱ ይጐዳል፤ የሚጠሉኝም ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።”
ከዚያም በብር የተለበጡትን ጣዖቶችህንና በወርቅ የተለበዱ ምስሎችህን ታዋርዳለህ፤ “ከዚህ ወግዱ!” ብለህም እንደ መርገም ጨርቅ ትጥላቸዋለህ።
እናንተ እስራኤላውያን ሆይ፤ እጅግ ወዳመፃችሁበት ወደ እርሱ ተመለሱ።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
“አዳኝ ወደ ጽዮን፣ ኀጢአታቸውንም ወደ ተናዘዙት ወደ ያዕቆብ ቤት ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር።
“በተጨማሪም ለዚህ ሕዝብ እንዲህ በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤
አንተና ሕዝብህ፣ እግዚአብሔር ለባቢሎን ንጉሥ አልገዛም ያለውን ሕዝብ ባስጠነቀቀበት በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት ለምን ታልቃላችሁ?
‘እኔ አልላክኋቸውም’ ይላል እግዚአብሔር ‘የሐሰት ትንቢት በስሜ ይናገራሉ፤ ስለዚህ እናንተንና ትንቢት የሚናገሩላችሁን ነቢያት አሳድዳለሁ፤ እናንተም ትጠፋላችሁ።’ ”
ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም እንዲሆንላቸው ዘወትር ይፈሩኝ ዘንድ፣ አንድ ልብ አንድም ሐሳብ እሰጣቸዋለሁ።
እናንተ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች፤ ለእግዚአብሔር ተገረዙ፤ የልባችሁንም ሸለፈት አስወግዱ፤ አለዚያ ስለ ሠራችሁት ክፋት፣ ቍጣዬ እንደ እሳት ይንበለበላል፤ ሊገታውም የሚችል የለም።
እኔም፣ ‘ይህን የምጠላውን አስጸያፊ ነገር አታድርጉ’ በማለት አገልጋዮቼን ነቢያትን ደጋግሜ ላክሁባቸው።
የማያወላውል ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ አዲስ መንፈስ በውስጣቸው አኖራለሁ፤ ድንጋዩን ልብ ከውስጣቸው አወጣለሁ፤ ሥጋ ልብም እሰጣቸዋለሁ።
እኔም፣ “እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብጽ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” አልኋቸው።
እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ! ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ! የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’
አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስ መንፈስም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።
ከእንግዲህ አመንዝራነታቸውንና ሕይወት የሌላቸውን የንጉሦቻቸውን ጣዖታት ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም በመካከላቸው ለዘላለም እኖራለሁ።
ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
“ዛፍ ሁሉ በፍሬው ስለሚታወቅ፣ መልካም ፍሬ እንድታገኙ መልካም ዛፍ ይኑራችሁ፤ መጥፎ ዛፍ ቢኖራችሁ ግን መጥፎ ፍሬ ታገኛላችሁ።
አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፤ አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጥ አጽዳ፤ ከዚያም ውጭው የጸዳ ይሆናል።
ጳውሎስና በርናባስም በድፍረት እንዲህ አሏቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገር አለበት፤ እናንተ ግን ናቃችሁት፤ በዚህም የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ ስለ ፈረዳችሁ፣ እኛም ወደ አሕዛብ ዞር ለማለት እንገደዳለን።
እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ።
እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ።
ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤
ስለዚህ ርኩሰትንና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ክፋትን አስወግዳችሁ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን፣ በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በትሕትና ተቀበሉ።
ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ።
ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ።
እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ፣ ለወንድሞቻችሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ።