ዕፍኝ ለማይሞላ ገብስና ለቍራሽ እንጀራ ስትሉ ሐሰትን የሚያደምጥ ሕዝቤን እየዋሻችሁ መሞት የማይገባውን በመግደል፣ መኖር የማይገባውንም በማትረፍ በሕዝቤ መካከል አርክሳችሁኛል።
በደለኛውን ማጽደቅ ሆነ፣ ጻድቁን በደለኛ ማድረግ፣ ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸው።
ልጄ ሆይ፤ እስኪ ምክርን ማዳመጥ ተው፤ ከዕውቀትም ቃል ትስታለህ።
አድልዎ ማድረግ መልካም አይደለም፤ ሰው ግን ለቍራሽ እንጀራ ሲል በደል ይፈጽማል።
ክፉውን መልካም፣ መልካሙን ክፉ ለሚሉ ብርሃኑን ጨለማ፣ ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ፣ ጣፋጩን መራራ፣ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!
እጅግ ሲበዛ ሆዳም ውሾች ናቸው፤ ጠገብሁን አያውቁም፤ የማያስተውሉ እረኞች ናቸው፤ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ሄዱ፤ እያንዳንዳቸውም የግል ጥቅማቸውን ፈለጉ።
በኢየሩሳሌም ባሉ ነቢያትም ላይ፣ የሚዘገንን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ፤ በመዋሸትም ይኖራሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ፣ የክፉዎችን እጅ ያበረታሉ፤ በእኔ ዘንድ ሁሉም እንደ ሰዶም፣ ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ናቸው።”
እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።
“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ የሕዝብን ነፍስ እንደ ወፍ በምታጠምዱበት አሸንክታብ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ከክንዳችሁ ላይ እቀዳድደዋለሁ፤ እንደ ወፍ የምታጠምዱትንም ሕዝብ ነጻ አወጣዋለሁ።
እኔ ያላሳዘንሁትን ጻድቅ በውሸት ስላሳዘናችሁ፣ ኀጢአተኛም ከክፉ መንገዱ ተመልሶ ሕይወቱን እንዳያድን በኀጢአቱ ስላበረታታችሁት፣
“ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።
መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ።
ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ፤ ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጐደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተምራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ።
በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈስሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ።
መሪዎቿ በጕቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቷ ለዋጋ ሲሉ ያስተምራሉ፤ ነቢያቷም ለገንዘብ ይጠነቍላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈውም፣ “እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ምንም ዐይነት ክፉ ነገር አይደርስብንም” ይላሉ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣ ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤ ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣ ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።
“በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳት እንዳታነድዱ፣ ምነው ከእናንተ አንዱ የቤተ መቅደሱን ደጅ በዘጋ ኖሮ! እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቍርባን አልቀበልም” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ወንድምህ በምትበላው ምግብ የሚያዝን ከሆነ፣ በፍቅር አልተመላለስህም፤ ክርስቶስ የሞተለትን ወንድምህን በመብልህ አታጥፋው።
እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ሆድ ነው። በለሰለሰ አንደበታቸውና በሽንገላ የዋሆችን ያታልላሉ።
ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው።
በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤
ሳኦልም አገልጋዩን፣ “መሄዱን እንሂድ፤ ነገር ግን ለሰውየው ምን እንሰጠዋለን? በስልቻዎቻችን የያዝነው ስንቅ ዐልቋል። ለእግዚአብሔር ሰው የምናበረክተውም ስጦታ የለንም፤ ታዲያ ምን አለን?” አለው።