“ስለዚህ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአሕዛብ መካከል እሰበስባችኋለሁ፤ ከተበተናችሁባቸው አገሮች እመልሳችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደ ገና እሰጣችኋለሁ።’
ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ፣ ከየአገሩ የሰበሰባቸው እንዲህ ይናገሩ።
ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤ ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣ የእጆቼ ሥራ፣ እኔ የተከልኋቸው ቍጥቋጦች ናቸው።
“የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ ከዚህ ስፍራ ወደ ባቢሎናውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳ ምርኮ በመልካም አስበዋለሁ።
ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።
እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹም ልባቸውም ወደ እኔ ስለሚመለሱ፣ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።
ሂድና ይህን መልእክት ወደ ሰሜን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ “ ‘ከዳተኛዪቱ እስራኤል ሆይ፤ ተመለሽ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ መሓሪ ስለ ሆንሁ፣ ከእንግዲህ በቍጣ ዐይን አላይሽም’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ለዘላለም አልቈጣም።
በዚያ ዘመን የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት በአንድነት ሆነው ከሰሜን ምድር ለአባቶቻቸው ርስት አድርጌ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይመጣሉ።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ ‘እነሆ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማዪቱ በፍርስራሿ ጕብታ ላይ ትሠራለች፤ ቤተ መንግሥቱም በቀድሞ ቦታው ይቆማል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ድምፅሽን ከልቅሶ፣ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክይ፤ ድካምሽ ያለ ዋጋ አይቀርምና፤” ይላል እግዚአብሔር። “ከጠላት ምድር ይመለሳሉ፤
ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ።
ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።
ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤልን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች መካከል በምሰበስብበት ጊዜ፣ አሕዛብ እያዩ ቅድስናዬን በመካከላቸው እገልጣለሁ፤ ከዚያም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ፤ ይህም ለባሪያዬ ለያዕቆብ የሰጠሁት ነው።
“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም።
ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።
“ ‘ከአሕዛብ መካከል አስወጣችኋለሁ፤ ከየአገሩ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራችሁም መልሼ አመጣችኋለሁ።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቤን ከምሥራቅና ከምዕራብ አገር እታደጋለሁ።
አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልስልሃል፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል።