ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የሰው መልክ የሚመስል ነበር።
ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።
አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ይሆናል።
የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ወለል ነበር።
“አንቺ የተጨነቅሽ ከተማ ሆይ፤ በዐውሎ ነፋስ የተናወጥሽ፣ ያልተጽናናሽም፤ እነሆ፤ በከበሩ ድንጋዮች አስጊጬ እገነባሻለሁ፤ በሰንፔር ድንጋይም እመሠርትሻለሁ።
ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
ከሕያዋኑ ፍጡራን ራስ በላይ የሚያስፈራና፤ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር።
በእሳቱም ውስጥ የአራት ሕያዋን ፍጡራን አምሳያ ነበረ፤ መልካቸውም የሰው ቅርጽ ይመስል ነበር።
እኔም አየሁ፤ እነሆ ከኪሩቤል ራስ በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ፣ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበረ።
ያ ሰው በአጠገቤ ቆሞ ሳለ፣ ከቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲናገረኝ ሰማሁ፤
እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ የዙፋኔ መቀመጫ የእግሬም ጫማ ማሳረፊያ ነው፤ በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም የምኖርበትም ስፍራ ነው። የእስራኤል ቤትም ሆኑ ነገሥታታቸው በአመንዝራነታቸውና በማምለኪያ ኰረብታቸው ላይ በሚያመልኳቸው፣ ሕይወት በሌላቸው በነገሥታታቸው ጣዖታት ከእንግዲህ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም።
እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ የሰውን ልጅ የሚመስል ነበረ፤ ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ታች እንደ እሳት ያለ ነበር፤ ወገቡንም ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ እንደ ጋለ ብረት ያበራ ነበር።
እንደ ገናም፣ ሰው የሚመስለው ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም።
ሥልጣን፣ ክብርና ታላቅ ኀይል ተሰጠው፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ መንግሥታትና ሕዝቦች ሰገዱለት፤ ግዛቱም ለዘላለም የማያልፍ ነው፤ መንግሥቱም ፈጽሞ የማይጠፋ ነው።
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው፤ ክብርን ይጐናጸፋል፤ በዙፋኑ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል የሰላም ምክር ይኖራል።’
“እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።
ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህም አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤
ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤ “አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ይሆናል።
የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤
ኢያሱ በኢያሪኮ አጠገብ ሳለ፣ ቀና ብሎ ሲመለከት የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ከፊቱ ቆሞ አየ። ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ፤ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ሲል ጠየቀው።
እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።
በመቅረዞቹም መካከል “የሰው ልጅ የሚመስል” አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ የሚደርስ መጐናጸፊያ የለበሰ፣ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።
አየሁም፤ እነሆ፤ በፊቴ ነጭ ደመና ነበረ፤ በደመናውም ላይ፣ “የሰውን ልጅ የሚመስል” ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል ደፍቶ፣ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር።
ከዚህ በኋላ ታላቅ ነጭ ዙፋንና በርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይ ከፊቱ ሸሹ፤ ስፍራም አልተገኘላቸውም።
እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋራ በርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋራ በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።
ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”