ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።”
“ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎች በረከት ትሆናለህ።
እግዚአብሔርም ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ።
በዚያ ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤
ወደ ውጭም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስኪ መቍጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቍጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው።
ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው።
ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ።”
እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና፣
በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤
ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ።
ከጕዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣ እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤ እነርሱም በስሜ፣ በአባቶቼ በአብርሃምና በይሥሐቅ ስም ይጠሩ፤ በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።”
“እግዚአብሔር ለእናንተና ለቀደሙት አባቶቻችሁ በመሐላ በሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ ከነዓናውያን አገር በሚያስገባችሁና ምድሪቱንም ለእናንተ በሚሰጣችሁ ጊዜ፣
እግዚአብሔር ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ።
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አንተና ከግብጽ ያወጣኸው ሕዝብህ ይህን ስፍራ ለቅቃችሁ ‘ለዘርህ እሰጣለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ገባሁላችሁ ምድር ሂዱ።
በዚያ ጊዜ ከያዕቆብ ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ከይሥሐቅም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን፣ ደግሞም ከአብርሃም ጋራ የገባሁትን ኪዳኔን ዐስባለሁ፤ ምድሪቱንም ዐስባታለሁ።
አምላካችሁ እግዚአብሔር ቍጥራችሁን ጨምሯል፤ ስለዚህ ዛሬ እናንተ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችኋል።
ነገር ግን እናንተን በብርቱ እጅ ያወጣችሁ፣ ከባርነት ምድርና ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን መዳፍ የተቤዣችሁ፣ እግዚአብሔር እናንተን ስለ ወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ ነው።
ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይሥሐቅንና ያዕቆብን ዐስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት።
እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤