“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብጽ መጻተኛ ነበራችሁና።
በድኻ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁን? ወይስ ወዳጃችሁን ትሸጣላችሁን?
እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድኻ አደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
“ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
“መጻተኛውን አትጨቍን፤ በግብጽ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።
መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፣ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕንና ጽድቅን አድርጉ፤ የተበዘበዘውን ከጨቋኙ እጅ አድኑት፤ መጻተኛውን፣ ወላጅ የሌለውንና መበለቲቱን አትበድሉ፤ አትግፏቸውም፤ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም አታፍስሱ።
መጻተኛውንና ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱንም ባትጨቍኑ፣ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደም ባታፈስሱ፣ የሚጐዷችሁን ሌሎች አማልክት ባትከተሉ፣
አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ፤ መጻተኞች ተጨቈኑ፤ ድኻ አደጎችና መበለቶች ተንገላቱ።
“ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም። “ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።
“ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ ዐብሯችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤
ዐብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብጽ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
“ ‘በመካከልህ ከወገንህ አንዱ ቢደኸይ፣ ራሱንም መርዳት ባይችል፣ በመካከልህ ይኖር ዘንድ መጻተኛውን ወይም እንግዳውን እንደምትረዳ ርዳው።
መበለቲቱን ወይም ድኻ አደጉን፣ መጻተኛውን ወይም ድኻውን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ።’
“ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
በዚያ ጊዜም ዳኞቻችሁን እንዲህ ስል አዘዝኋቸው፤ “በወንድሞቻችሁ መካከል የሚነሣውን ክርክር ያለ አድልዎ እዩት፤ ሙግቱ ወንድማማች በሆኑ እስራኤላውያን መካከል ወይም በአንድ እስራኤላዊና በመጻተኛ መካከል ቢሆን፣ በጽድቅ ፍረዱ።
እርሱ አባት ለሌላቸውና ለመበለቶች ይፈርዳል፤ መጻተኛውንም ምግብና ልብስ በመስጠት ይወድዳል።
ስለዚህ እናንተም በግብጽ ምድር መጻተኞች ነበራችሁና መጻተኛን ውደዱ።
አንተም ራስህ በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን ትእዛዝ ዛሬ የምሰጥህም በዚሁ ምክንያት ነው።
ደስ በሚያሠኘው ቦታና ራሱ በመረጠው ከተማ በመካከልህ ይኑር፤ አንተም አታስጨንቀው።
ወንድምህ ስለ ሆነ ኤዶማዊውን አትጸየፈው፤ መጻተኛ ሆነህ በአገሩ ኖረሃልና ግብጻዊውን አትጥላው።
ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ።
“በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።