እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ጋራ ስናገር ሕዝቡ እንዲሰሙኝና እምነታቸውን ምን ጊዜም በአንተ ላይ እንዲጥሉ በከባድ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” ከዚያም ሙሴ ሕዝቡ ያሉትን ለእግዚአብሔር ነገረው።
ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤
በማግስቱም ጧት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ ስሙኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።
ደመናና ጥቅጥቅ ያለ ጭጋግ በዙሪያው አለ፤ ጽድቅና ፍትሕ የዙፋኑ መሠረት ናቸው።
ከደመና ዐምድ ውስጥ ተናገራቸው፤ እነርሱም ትእዛዙንና የሰጣቸውን ድንጋጌ ጠበቁ።
እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሙሴም አመኑ።
በሦስተኛውም ቀን ጧት ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጐድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ።
እግዚአብሔር ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።
ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወረደ፤ በዚያም ከርሱ ጋራ ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን ዐወጀ።
ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኛቸውና መከራቸውን እንዳየ በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።
እግዚአብሔርም “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው።
ስለ ግብጽ የተነገረ ንግር፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጻውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፣ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ ”
ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ዐምድ ወረደ፤ በድንኳኑም ደጃፍ ቆሞ አሮንንና ማርያምን ጠራቸው፤ ሁለቱም ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፣
እርሱ እየተናገረ ሳለ፣ ብሩህ ደመና ሸፈናቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “በርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ ተሰማ።
ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ።
“እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተን የማይቀበል እኔን አይቀበልም፤ እኔንም የማይቀበል የላከኝን አይቀበልም።”
“በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ።
ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ።
“እነሆ፤ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሳይቀሩ፣ ዐይን ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ ከርሱ የተነሣ ዋይ ዋይ ይላሉ።” አዎ! ይህ ሁሉ ይሆናል። አሜን።