ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬዪቱ ምሽት ታውቃላችሁ።
በሙሴና በአሮን እጅ፣ ሕዝብህን እንደ በግ መንጋ መራኸው።
“ሕዝቤ ግን አላደመጠኝም፤ እስራኤልም እጅ አልሰጥ አለኝ።
በዚያችው ዕለት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው አድርጎ ከግብጽ ምድር አወጣቸው።
እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብጽ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው።
ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቷልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” አላቸው።
ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ እንደ ቈየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት።
ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብጽ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነድዳል?
ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ” አለው።
“ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብጻውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ።
የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብጻውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ።
ሙሴም እንዲህ አለ፤ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዳደርግ እግዚአብሔር እንደ ላከኝና ከራሴም እንዳይደለ በዚህ ታውቃላችሁ፤
ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ፈጽሞ አዲስ የሆነ ነገር አምጥቶ ምድር አፏን ከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥና በሕይወታቸው ወደ መቃብር ቢወርዱ፣ ሰዎቹ እግዚአብሔርን የናቁ መሆናቸውን የምታውቁት ያን ጊዜ ነው።”