እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው።
እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ስነቃም ክብርህን አይቼ እረካለሁ።
እኔም ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አቀናለሁ፤ ፍጹም ደስታዬ ወደ ሆነው አምላክ እሄዳለሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፣ በበገና አመሰግንሃለሁ።
ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና።
ከርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤
እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።
ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ?
ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።
የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ ርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል።
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
እርሷም ሁሉን ነገር በሁሉም ረገድ የሚሞላው፣ የርሱ ሙላት የሆነች አካሉ ናት።
የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋራ የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው።
ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ።
ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤
በልቤ ስላላችሁ እና በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋራ የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው።
ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣
እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤
ነገር ግን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እደጉ። ለርሱ አሁንም፣ ለዘላለምም ክብር ይሁን! አሜን።