አምላክ ያደረገውን ሁሉ አየሁ። ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ማንም ሊያውቅ አይችልም፤ ሰው ለመመርመር ብዙ ቢጥርም፣ ትርጕሙን ማግኘት አይችልም፤ ጠቢብም እንኳ ዐውቀዋለሁ ቢል፣ ፈጽሞ ሊገነዘበው አይችልም።
እርሱ፣ የማይመረመሩ ድንቅ ነገሮች፣ የማይቈጠሩም ታምራት ያደርጋል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች።
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም።
ይህን ነገር ለመረዳት በሞከርሁ ጊዜ፣ አድካሚ ተግባር መስሎ ታየኝ።
ከሰማይ በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ ለማጥናትና ለመመርመር ራሴን አተጋሁ፤ አምላክ በሰዎች ላይ የጫነው እንዴት ያለ ከባድ ሸክም ነው!
የነፋስን መንገድ እንደማታውቅ፣ ሕይወት ወይም መንፈስ በእናት ማሕፀን ውስጥ ወደሚገኘው አካል እንዴት እንደሚገባም እንደማታውቅ ሁሉ፣ ሁሉን ሠሪ የሆነውን፣ የአምላክን ሥራ ማስተዋል አትችልም።
ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ አምላክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።
አምላክ ያደረገውን ተመልከት፤ እርሱ ያጣመመውን፣ ማን ሊያቃናው ይችላል?
አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።
የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!