እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ አምላክን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።
እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና” አለው።
የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ፤ የምታደርገው ሁሉ እንዲከናወንልህ፣ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲሳካልህ፣ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው በመንገዶቹ ተመላለስ፣ ሥርዐቶቹንና ትእዛዞቹን፣ ሕጎቹንና ደንቦቹን ጠብቅ፤
ከዚያም ሰውን፣ ‘እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው’ አለው።”
እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።
ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።
ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል።
እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤ ቂሎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።
እግዚአብሔርን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤ እንዲህ ያለውም ሰው እፎይ ብሎ ያርፋል፤ መከራም አያገኘውም።
ልብህ በኀጢአተኞች አይቅና፤ ነገር ግን ዘወትር እግዚአብሔርን ለመፍራት ትጋ።
አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሠኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በዐጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደ ሆነ ለማየት ፈለግሁ።
አምላክ ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ይህን አደረገ።
ብዙ ሕልምና ብዙ ቃል ከንቱ ነው፤ ስለዚህ አምላክን ፍራ።
ሰው በሕይወት ሳለ፣ እንደ ጥላ በሚያልፉት ጥቂትና ከንቱ በሆኑት ቀኖቹ፣ ለሰው መልካም የሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? እርሱ ከሄደ በኋላስ ከፀሓይ በታች የሚሆነውን ማን ሊነግረው ይችላል?
አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤ አምላክን የሚፈራ ሰው ጽንፈኛነትን ያስወግዳል።
ኀጥእ መቶ ወንጀል ሠርቶ ዕድሜው ቢረዝምም፣ አምላክን የሚያከብሩ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው ዐውቃለሁ።
እርሱን የሚታዘዝ ሁሉ አይጐዳም፤ ጥበበኛም ልብ ትክክለኛውን ጊዜና ተገቢውን አሠራር ያውቃል።
ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?
ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣
አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ አምልከውም፤ ከርሱም ጋራ ተጣበቅ፤ በስሙም ማል።
“በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ።
ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ጠብቁ።
ይኸውም፣ የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ ነው።
ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።
ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ፤ “እናንተ ባሮቹ ሁሉ፣ እርሱን የምትፈሩ፣ ታናናሾችና ታላላቆችም፣ አምላካችንን አመስግኑ!”
ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ልባችሁ በታማኝነት አምልኩት፤ ያደረገላችሁንም ታላላቅ ነገሮች አትርሱ።