“በምድሪቱ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ እኔን ማክበር እንዲማሩ፣ ለልጆቻቸውም እንዲያስተምሩ ቃሌን ይሰሙ ዘንድ ሕዝቡን በፊቴ ሰብስብ” ባለኝ ጊዜ፣ በኮሬብ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቆማችሁበትን ዕለት አስታውሱ።
ትክክለኛና ጽድቅ የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።”
ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ያስተጋባል፤ ብርቱ ሥራህን ያውጃል።
በሦስተኛው ወር እስራኤላውያን ከግብጽ ለቅቀው በወጡበት በዚያችው ዕለት ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።
በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በዚያ ቀን በሕዝቡ ፊት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል።
በሦስተኛውም ቀን ጧት ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጐድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ።
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ጋራ ስናገር ሕዝቡ እንዲሰሙኝና እምነታቸውን ምን ጊዜም በአንተ ላይ እንዲጥሉ በከባድ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” ከዚያም ሙሴ ሕዝቡ ያሉትን ለእግዚአብሔር ነገረው።
ሕዝቡም መብረቁንና ነጐድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሀት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤
ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሀት ከእናንተ ጋራ ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው።
እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ አምላክን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።
እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል። ስለ አንተ ታማኝነትም፣ አባቶች ለልጆቻቸው ይነግራሉ።
ምሕረቱም ለሚፈሩት ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።
የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር፣ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዐቶችና ሕግጋት እነዚህ ናቸው።
ምን ጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብላ።
አምላኩን እግዚአብሔርን ማክበር ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉና ይህን ሥርዐት በጥንቃቄ ይከተል ዘንድ ከርሱ ጋራ ይሁን፤ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ያንብበው።
ዐይኖቻችሁ ያዩአቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ። እነዚህን ለልጆቻችሁና ከእነርሱ በኋላ ለሚወለዱት ልጆቻቸው አስተምሯቸው።
አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቷል።
ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
ይኸውም፣ የምሰጣችሁን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ በመጠበቅ፣ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም፣ አንተ፣ ልጆችህና ከእነርሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቻቸው በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትፈሩት ዘንድ ነው።
ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።
የሚናገረውን እርሱን እንቢ እንዳትሉት ተጠንቀቁ። እነዚያ ከምድር ሆኖ ሲያስጠነቅቃቸው የነበረውን እንቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፣ እኛ ከሰማይ የመጣው ሲያስጠነቅቀን ከርሱ ብንርቅ እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?
ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ፤ “እናንተ ባሮቹ ሁሉ፣ እርሱን የምትፈሩ፣ ታናናሾችና ታላላቆችም፣ አምላካችንን አመስግኑ!”
ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ በፍጹም ልባችሁ በታማኝነት አምልኩት፤ ያደረገላችሁንም ታላላቅ ነገሮች አትርሱ።