ጠላቶችህን ለመውጋት ወደ ጦርነት ስትሄድ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ከአንተ የሚበልጥ ሰራዊትንም በምታይበት ጊዜ አትፍራቸው፤ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና።
ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ።
አሳም ሊገጥመው ወጣ፤ መሪሳ አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆም የውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ።
በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ደካሞችን ከኀይለኞች የሚታደግ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።”
አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ ዐቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም፤ ነገር ግን ዐይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።”
እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡ።
እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
እነዚህ በሠረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክሕታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው።
በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ ብሄድ እንኳ፣ አንተ ከእኔ ጋራ ስለ ሆንህ፣ ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ፣ እነርሱ ያጽናኑኛል።
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ የያዕቆብም አምላክ መጠጊያችን ነው። ሴላ
ኑና የእግዚአብሔርን ሥራ፣ ምድርንም እንዴት ባድማ እንዳደረጋት እዩ።
“ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።
ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብጽ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው!
እኔ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።
በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።
ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች።
“ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤
ጠላትን መንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ ይረጋግጣሉ፤ በአንድነት እንደ ጦር ሰልፈኛ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ስለ ሆነ ተዋግተው፤ ፈረሰኞችን ያዋርዳሉ።
በገዛ ምድራችሁ በግፍ በመጣባችሁ ጠላት ላይ ስትዘምቱ መለከቶቹን ከፍ ባለ ድምፅ ንፉ፤ በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ትታሰባላችሁ፤ ከጠላታችሁም እጅ ትድናላችሁ።
“በያዕቆብ መጥፎ ነገር አልተገኘም፤ በእስራኤልም ጕስቍልና አልታየም፤ እግዚአብሔር አምላኩ ከርሱ ጋራ ነው፤ የንጉሡም እልልታ በመካከላቸው ነው።
ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?
እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም።
አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኳችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጕዞ ጠብቋችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።
ወደ ውጊያው ቦታ ስትቃረቡ፣ ካህኑ ወደ ፊት ወጣ ብሎ ለሰራዊቱ ይናገር፤
እንዲህም ይበል፤ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ በዛሬው ቀን ጠላቶቻችሁን ለመግጠም ወደ ጦርነት ልትገቡ ነው፤ ልባችሁ አይባባ፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ በጠላቶቻችሁ ፊት አትሸበሩ፤
ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”
እግዚአብሔር ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋራ ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”
አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣
ነገር ግን አትፍራቸው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብጽ ሁሉ ላይ ያደረገውን በሚገባ አስታውስ።
በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና የሚያስፈራ አምላክ ስለ ሆነ አያስደንግጡህ።
ይሁን እንጂ እንደሚባላ እሳት ከፊትህ ቀድሞ የሚሻገረው አምላክህ እግዚአብሔር መሆኑን ዛሬ ርግጠኛ ሁን፤ እነርሱን ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ድል ያደርጋቸዋል፤ አንተም እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ታስወጣቸዋለህ፤ በፍጥነትም ትደመስሳቸዋለህ።
በሕይወት በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋራ እንደ ነበርሁ ሁሉ ከአንተም ጋራ እሆናለሁ፤ ከቶ አልጥልህም፤ አልተውህም።
በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋራ ነውና አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና፤ አትፍራ፤ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?”
ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም አቃጠለ።
የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው” አለው።
እግዚአብሔርም፣ “በርግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው።
ዳዊትም ሳኦልን፣ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ ባሪያህ ሄዶ ይዋጋዋል” አለው።