ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቃል የመስማት ራብ እንጂ፣ እንጀራን የመራብ ወይም ውሃን የመጠማት አይደለም።
እስራኤል ያለ እውነተኛ አምላክ፣ ያለ አስተማሪ ካህንና ያለ ሕግ ብዙ ዘመን አሳልፈዋል።
የምናየው ምልክት የለም፤ ከእንግዲህ የሚነሣ አንድም ነቢይ የለም፤ ይህ እስከ መቼ እንደሚቀጥል የሚያውቅ በእኛ ዘንድ የለም።
ራእይ በሌለበት ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተባረከ ነው።
የማይኰተኰትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኵርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት ደመናዎችን አዝዛለሁ።”
ጥፋት በጥፋት ላይ፣ ወሬም በወሬ ላይ ይመጣል። ራእይን ከነቢይ ለማግኘት ይጥራሉ፤ የሕግ ትምህርት ከካህኑ፣ ምክርም ከሽማግሌው ዘንድ ይጠፋል።
አለዚያ ገፍፌ ዕርቃኗን አስቀራታለሁ፤ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፤ እንደ ምድረ በዳ፣ እንደ ደረቅም ምድር አደርጋታለሁ፤ በውሃ ጥምም እገድላታለሁ።
ስለዚህ ሌሊቱ ያለ ራእይ፣ ጨለማውም ያለ ሟርት ይመጣባችኋል፤ በነቢያት ላይ ፀሓይ ትጠልቅባቸዋለች፤ ቀኑም ይጨልምባቸዋል።
ሕዝቡም እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ ዐዘነላቸው።
ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “አስነሥተህ የምታውከኝ ለምንድን ነው?” አለው። ሳኦልም፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ፍልስጥኤማውያን እየወጉኝ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ” አለው።
እርሱም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔር ግን በሕልምም ሆነ በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።
ብላቴናው ሳሙኤል ከዔሊ በታች ሆኖ እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር። በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ብርቅ ነበረ፤ ራእይም አይታይም ነበር።