የእግዚአብሔርን ቀን ለምትሹ፣ ለእናንተ ወዮላችሁ! የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትሻላችሁ? ያ ቀን ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም።
የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና አልቅሱ፤ ሁሉን ቻይ ከሆነ አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣልና።
ከሽብር ድምፅ የሚሸሽ፣ ወደ ጕድጓድ ይገባል፤ ከጕድጓድ የወጣም፣ በወጥመድ ይያዛል። የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፤ የምድርም መሠረት ተናወጠ።
“በዐይናችን እንድናይ እግዚአብሔር ይቸኵል፤ ሥራውንም ያፋጥን፤ የእስራኤልን ቅዱስ፣ የርሱን ዕቅድ እንድናውቃት ትቅረብ፤ ትምጣም” ለሚሉ ወዮላቸው!
በዚያ ቀን እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤ ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፣ ጨለማንና መከራን ያያል፤ ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል።
ዕለት በዕለት ይፈልጉኛል፤ መንገዴን ለማወቅ የሚጓጉ ይመስላሉ፤ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ፣ የአምላኩንም ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ሁሉ፣ ተገቢ የሆነ ፍትሕ ይለምኑኛል፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ እንዲቀርብ የሚወድዱም ይመስላሉ።
ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታሉ፣ የሚያዩትም ጭንቀት፣ ጨለማና የሚያስፈራም ጭጋግ ብቻ ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ።
በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ትጋያለች፤ ሕዝቡም እሳት ውስጥ እንደሚጨመር ማገዶ ይሆናል፤ ወንድሙንም ማዳን የሚችል ማንም የለም።
ጨለማን ሳያመጣ፣ በሚጨልሙትም ተራሮች ላይ፣ እግሮቻችሁ ሳይሰናከሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ፤ እርሱ ወደ ጨለማ ይለውጠዋል፤ ድቅድቅ ጨለማም ያደርገዋል።
እነርሱ ደጋግመው፣ “የእግዚአብሔር ቃል የት አለ? እስኪ አሁን ይፈጸም!” ይሉኛል።
ወዮ ለዚያ ቀን! እንደዚያም ያለ አይኖርም፤ ለያዕቆብ የመከራ ጊዜ ነው፤ ነገር ግን ይተርፋል።
“የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር፣ ‘ዘመኑ ረዝሟል፤ ራእዩ ሁሉ ከንቱ ሆኗል’ የምትሉት ይህ አባባል ምንድን ነው?
“የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት፣ ‘ይህ ሰው የሚያየው ራእይ ገና ለሩቅ ዘመን የሚሆን ነው፤ የሚናገረውም ትንቢት የረዥም ጊዜ ትንቢት ነው’ ይላሉ።
ወዮ ለዚያ ቀን! የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤ ከሁሉን ቻይ አምላክ እንደ ጥፋት ይመጣል።
ምድር በፊታቸው ትንቀጠቀጣለች፤ ሰማይም ይናወጣል፤ ፀሓይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤ ከዋክብትም ከእንግዲህ ወዲያ አያበሩም።
በሰራዊቱ ፊት፣ እግዚአብሔር ያንጐደጕዳል፤ የሰራዊቱ ብዛት ስፍር ቍጥር የለውም፤ ትእዛዙንም የሚያደርግ እርሱ ኀያል ነው፤ የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ፣ እጅግም የሚያስፈራ ነው፤ ማንስ ሊቋቋመው ይችላል?
ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፤ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች።
“በአሕዛብ ሁሉ ላይ፣ የእግዚአብሔር ቀን ደርሷል፤ አንተ እንዳደረግኸው፣ በአንተም ላይ ይደረጋል፤ ክፉ ሥራህም በራስህ ላይ ይመለሳል።
“እነሆ፤ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አያስቀርላቸውም።
የሚያጠፋ ራብ፣ በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድ መቅሠፍት እሰድድባቸዋለሁ፤ የአራዊትን ሹል ጥርስ፣ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝም እሰድድባቸዋለሁ።
የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል።
እነርሱም፣ “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” ይላሉ።