በነጋም ጊዜ፣ አይሁድ ተሰብስበው በማሤር ጳውሎስን እስኪገድሉ ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማማሉ። በዚህ ሤራ
ወንድሞቹም ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲመጣ በሩቅ አዩት፤ ወደ ነበሩበትም ስፍራ ከመድረሱ በፊት ሊገድሉት ተማከሩ።
ስለዚህም እርሷ፣ “ነገ በዚህ ሰዓት ያንተንም ነፍስ ከእነዚያ እንደ አንዱ ነፍስ ሳላደርጋት ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ” ስትል ወደ ኤልያስ መልእክተኛ ላከች።
ንጉሡም፣ “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በዐንገቱ ላይ ካደረ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ዛተ።
እነርሱም ከወንድሞቻቸውና ከመኳንንታቸው ጋራ በመሆን በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ የጌታችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች፣ ደንቦችና ሥርዐቶች ሁሉ ለመታዘዝ በዚህ ርግማንና መሐላ ቃል ገቡ።
መርዶክዮስም አድማውን ስለ ደረሰበት፣ ለንግሥት አስቴር ገለጸላት፤ እርሷም ይህን ከመርዶክዮስ ማግኘቷን ለንጉሡ ገልጻ ነገረችው።
የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤ ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤ በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣ ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ።
እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት ነበርሁ፤ እነርሱም፣ “ዛፉን ከፍሬው ጋራ እንቍረጥ፤ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው፤ ከእንግዲህም ወዲያ ስሙ አይታሰብ” ብለው እንዳደሙብኝ ዐላወቅሁም ነበር።
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተና ሚስቶቻችሁ፣ “ለሰማይዋ ንግሥት ለማጠንና የመጠጥ ቍርባን ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በርግጥ እንፈጽማለን” ብላችሁ የገባችሁትን ቃል በተግባር አሳይታችኋል።’ “እንግዲያውስ ወደ ኋላ አትበሉ፤ ቃል የገባችሁትን፣ ስእለታችሁንም ፈጽሙ።
“ ‘እንዲጠፋ የተወሰነ ማንኛውም ሰው አይዋጅም፤ መገደል አለበት።
በረቀቀ መንገድ ኢየሱስን ለማስያዝና ለማስገደል ተማከሩ።
እርሱም እየማለና እየተገዘተ፣ “እኔ ሰውየውን አላውቀውም!” አላቸው። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።
ሕዝቡም በሙሉ፣ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን!” ብለው መለሱ።
የተማማሉትም ከአርባ በላይ ነበሩ።
እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ጳውሎስን ሳንገድል እህል ላለመቅመስ ጽኑ መሐላ አድርገናል።
ስለዚህ ዕሺ አትበላቸው፤ ምክንያቱም ከመካከላቸው ከአርባ በላይ የሚሆኑት ሊገድሉት አድፍጠው እየጠበቁት ነው፤ ደግሞም እስኪገድሉት ድረስ እህል ውሃ ላለመቅመስ ተማምለዋል፤ አሁንም ተዘጋጅተው የአንተን መልስ እየተጠባበቁ ነው።”
አይሁድ ግን በዚህ ሰው ላይ ማሤራቸውን በተረዳሁ ጊዜ፣ ወዲያው ወደ አንተ ላክሁት፤ ከሳሾቹም ከርሱ ጋራ ያላቸውን ክርክር ለአንተ እንዲያቀርቡ አዘዝኋቸው።
ጳውሎስን መንገድ ላይ አድፍጠው ሊገድሉት ስለ ፈለጉ፣ ፊስጦስ ለእነርሱ እንዲያዳላላቸውና ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስመጣው አጥብቀው ለመኑት።
ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤
ሳውል ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤
ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታ ሆይ፤ ና!
ብዙ ጊዜ በጕዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር።
“በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል።
ይኸውም ይድኑ ዘንድ ለአሕዛብ እንዳንናገር ለመከልከል ነው፤ በዚህ ሁኔታ ኀጢአታቸውን ሁልጊዜ በራሳቸው ላይ እስከ መጨረሻው እያከማቹ ይሄዳሉ። ቍጣውም በእነርሱ ላይ ያለ ልክ መጥቷል።
በዚያ ጊዜም ኢያሱ፣ እንዲህ ሲል ማለ፤ “ይህች ከተማ ኢያሪኮን መልሶ የሚሠራት ሰው በእግዚአብሔር ፊት የተረገመ ይሁን፤ “መሠረቷን ሲጥል፣ የበኵር ልጁ ይጥፋ፤ ቅጥሮቿንም ሲያቆም፣ የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ” ብሎ ማለ።
እስራኤላውያን ግን ዕርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ ዕርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።
ዕርሙ የተገኘበት ሰው፣ እርሱና ያለው ሁሉ በእሳት ይቃጠላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን አፍርሷል፤ በእስራኤልም ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ፈጽሟልና።’ ”
ሳኦል፣ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አምሎ ስለ ነበር፣ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።